የሸገር ከተማ አስተዳደር የመሬት ሀብት ምዝገባ እያካሄደ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሸገር ከተማ አስተዳደር የመሬት ሀብት ምዝገባ እያካሄደ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ ግንቦት 02/2015(ኢዜአ):- የሸገር ከተማ አስተዳደር የተሟላ መረጃ መያዝ የሚያስችል የመሬት ሀብት ምዝገባ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።
የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ ለኢዜአ እንደገለጹት ከተማው ከተመሰረተ ጀምሮ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ አስተዳደርና አወቃቀር እንዲኖረው የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።
ከስራዎቹ መካከል በከተማው ምን ያህል እና ምን አይነት መሬት እንዳለ ለማወቅ የተሟላ መረጃ መያዝ የሚያስችል የመሬት ምዝገባ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
'ላንድ ኢንቨንተሪ' በተሰኘ የመመዝገቢያ ስርዓት እየተካሄደ ያለው ስራ ትክክለኛ የመሬት ሀብት መረጃ መያዝ የሚያስችል ነው ብለዋል።
አሰራሩ ከዘመናዊ የመሬት ምዝገባ ስርዓት (ካዳስተር ስርዓት) ጋር ጎን ለጎን እየተተገበረ መሆኑንና ምዝገባው በከተማ አስተዳደሩ ሁሉም ክፍለ ከተሞች እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁን በተከናወነው ስራ ከ250 ሺህ በላይ "ቁራጭ መሬቶችን" (piece of lands) በትክክል መመዘገብ እንደተቻለ አንስተው፤ ይህም ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት ከንቲባው።
ምዝገባው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ተሾመ፤ መሬቱ ላይ ምን እንዳለ በቅርበት የሚያሳይ የሳተላይት መረጃ ጭምር በምዝገባው መካተቱን ገልጸዋል።
ለዚሁ ስራ በእያንዳንዱ የሸገር ክፍለ ከተሞች በተመሳሳይ 20 የመሬት ባለሙያዎች ተመድበው ምዝገባውን እያካሄዱ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
"የመሬት ምዝገባ ስራው ሲጠናቀቅ በከተማ አስተዳደሩ ከሕገ ወጥ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ጋር የሚያያዙ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላል ብለዋል" ዶክተር ተሾመ።
"በከተማው በሕገ ወጥ መንገድ የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች ለማህበረሰቡም ይሁን ለከተማው ችግር ናቸው፤ በሕገ ወጥ መልኩ በወረራ በተገነቡ መንደሮች መሰረታዊ አገልግሎት የሌለበት አስቸጋሪ ሁኔታ አለ" ሲሉ ገልጸዋል።
ከተማው ከተመሰረተበት ግብ አንጻርም "ሕገ ወጥ ግንባታዎችን የማስቆምና የመከላከል ስራ" በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ዶክተር ተሾመ ገለጻ፤ "በቀጣይ በከተማው በዘላቂነት ሕጋዊነትን የማጠናከር ስራዎች በትኩረት ይሰራል፤ የሕግ የበላይነት የምታከብርና የምታስከብር እንዲሁም አብሮነት የተጠናከረባት ከተማ እንድትሆን ይሰራል" ብለዋል።
የሸገር ከተማ አስተዳደር በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ከተሞችን አንድ ላይ አቅፎ የያዘና በ12 ክፍለ ከተሞችና በ36 ወረዳዎች የተደራጀ መሆኑ ይታወቃል።