ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ለማስተሳሰር የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በቁርጠኝነት ትሰራለች - ዶክተር ዓለሙ ስሜ

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2015 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ለማስተሳሰር የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በቁርጠኝነት በመሥራት የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር ዓለሙ ስሜ ገለጹ፡፡   

የአንድ አፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ የሙከራ ትግበራ ፕሮጀክት ፍኖተ ካርታ ዙሪያ በአዲስ አበባ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ 
 

የውይይት መድረኩ የተዘጋጀው በአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የጋራ ትብብር ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል። 

 የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በተለይም በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ አህጉራዊ ትስስር መፍጠር ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል።

ለዚህም ሲባል የአንድ አፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ገበያ የሙከራ ትግበራ ፕሮጀክት ፍኖተ ካርታ ተቀርፆ የሙከራ ትግበራ ለመጀመር በሂደት ላይ ይገኛል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ በአዲስ አበባ በሚመክረው መድረክ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር ዓለሙ ስሜ፤ የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የአየር ትራንስፖርትን ጨምሮ በሁሉም መስክ አህጉራዊ ትስስር መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ አፍሪካን በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ለማስተሳሰር ለሚደረገው ጥረት በቁርጠኝነት እንደምትሰራና የመሪነት ሚናዋንም አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ አረጋግጠዋል።

አህጉራዊ የአየር ትራንስፖርት ትስስሩ መሳለጥ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ በተለይም ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ እድገት የላቀ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

አፍሪካውያን እምቅ የቱሪዝም ሃብታቸውን ለማስተዋወቅና ቱሪስቶችን ለመሳብም ለትራንስፖርት ዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

በመሆኑም በሁሉም መስክ አህጉራዊ ልማትና ዕድገትን ለማጠናከር ለሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሆና ትሰራለች ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር መንግስቱ ንጉሴ፤ ኢትዮጵያ የአንድ አፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ስምምነት መፈረሟን አስታውሰው፤ ለተግባራዊነቱም እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል። 

የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ አደፉንኬ አዴይሚ በበኩላቸው፤ የአፍሪካን የአየር ትስስር  ለማሳለጥና ገበያውን ለማነቃቃት በትብብር መሥራት ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፉ የአቪዬሽን ገበያ፣ ስመጥር አየር መንገድና አስተማማኝ መሰረተ-ልማት ያላት በመሆኑ በዘርፉ የላቀ አስተዋጽዖ አላት ነው ያሉት። 


 

ለጥገና፣ ለሥልጠና እና ለአቅም ግንባታ ሥራዎች እያደረገች ያለውን አስተዋጽዖ አድንቀዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የውይይት መድረክ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዘርፉ ያላቸውን ልምድ እንደሚያጋሩ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም