የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ስምንት ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ስምንት ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2015 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ስምንት ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉ የተደረገው በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን፣ሶማሌ ክልልና ደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን ለሚገኙ ዜጎች መሆኑን አመልክቷል።
የምግብ ዘይት፣ሩዝ፣ብስኩት፣ የእንጀራ ድርቆሽና የሕጻናት አልሚ ምግቦች ለዜጎቹ የተደረገ ድጋፍ ነው።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ድርጅት ፕሬዝዳንት ድጋፉን ለተወካዮች አስረክበዋል።
ሰራዊቱ ከሕዝብ አካል የተገኘ በመሆኑ ችግሩን እንደ ራሱ ችግር በመቁጠር በፍላጎቱ ከደመወዙ በማዋጣት በዝናብ እጥረት ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገልጸዋል።
ተቋሙ በቀጣይም በድርቅ የተጎዱ ወገኖች ከችግር ወጥተው ወደ ዘላቂ ልማት እስኪገቡ ድረስ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ድጋፍ ላሰባሰቡ አካላት ምስጋና አቅርበው እርዳታውን የተረከቡ አካላት በአግባቡ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ቁጥጥር እንዲያደርጉና አፈጻጸሙን እንዲከታተሉ ኮሚሽነር ጀነራሉ አሳስበዋል።
ለደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን የተደረገውን ድጋፍ የተረከቡት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሕዝብ ጋሻ ሆኖ ለሕዝብ ክብርና ለአገር ደህንነት በጀግንነት ዋጋ መክፈሉን አውስተዋል።
ከዚህም ባሻገር ወገን በዝናብ እጥረት ተጎድቶ የድረሱልኝ ጥሪ ሲያቀርብ ካለው ላይ ቀንሶ መርዳቱ እጅግ የሚያኮራ ተግባር ነው ብለዋል።
“ኢትዮጵያዊነት ይህ ነው፤ ከተረፈን ሳይሆን አንዳችን ለሌላችን እንደርሳለን በሚል በፍቅርና በመተሳሰብ ስሜት የተደረገው ድጋፍ ትልቅ አርአያነት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ለኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተደረገውን ድጋፍ የተረከቡት የኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ስራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ በበኩላቸው በክልሉ የተከሰተው ድርቅ በሰው ሕይወት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የክልሉ መንግስትና ሌሎች አካላት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሕዝብ ችግርን እንደ ራሱ ችግር ቆጥሮ ከደመወዙና ከሬሽኑ ቀንሶ ላደረገው ድጋፍ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው መሆኑን ከተቋሙ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።