የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነው- የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነው- የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2015(ኢዜአ) ፡-የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆኑን የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ አለሙ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አዋጅ ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ኮሚሽነሮችም ተሹመውለት ስራ መጀመሩ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ስራዎችን በምእራፍ ከፋፍሎ ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ ለመጀመር በሂደት ላይ መሆኑን መግለፃቸው ይታወሳል።
በሂደቱ በእያንዳንዱ ወረዳ ዘጠኝ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት እንደሚኖሩ ጠቅሰው እያንዳንዳቸው 50 ተወካዮቻቸውን የሚመርጡ መሆኑንም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።
በሂደቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱንም ይፋ አድርገዋል።
በመሆኑም ኮሚሽኑ እያከናወነ ያለውን ስራ ከማገዝና ሂደቱን ውጤታማ ከማድረግ አንፃር የፓርቲዎችን ዝግጁነት በማስመልከት ኢዜአ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ አለሙ ጋር ቆይታ አድርጓል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ችግሮችን መቋጫ ለማበጀት አገራዊ ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር መብራቱ በየትኛውም መልኩ እገዛና ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።
ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የጋራ ምክር ቤቱ የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት ስለመዘጋጀቱም አረጋግጠዋል።
በአገራዊ የምክክር ሂደቱ እንደ አገር እየፈተኑ ያሉ ዋና ዋና ችግሮችን በመለየት መነጋገርና የጋራ መፍትሄ ማበጀት እንዲሁም ምክክሩ እንዲሳካ የሁሉም ሃላፊነት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረጉ ማናቸውንም ህገ ወጥ ድርጊቶች መከላከልና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የጋራ ጥረታችን ሊታከልበት ይገባልም ነው ያሉት።
በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዚህ ቁርጠኛ በመሆን ሊሰሩ ይገባል ያሉት ዶክተር መብራቱ የጋራ ምክር ቤቱም የሚጠበቅትን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።