በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት - ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ - ኢዜአ አማርኛ
በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት - ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2015(ኢዜአ)፡-በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት አለበት ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ።
ቤተክርስቲያኗ ዓመታዊውን የርክበ-ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ-ጉባዔ በዛሬው ዕለት መጀመሩን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገልጸዋል።
ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጉባዔው የቤተክርስቲያኗ መደበኛ ተልዕኮን መሰረት አድርገው የተሰሩ ሥራዎችና ያጋጠሙ ችግሮች ይዳሰስበታል ብለዋል።
የቤተክርስቲያኗን ሰላም የመጠበቅ፣ የማስጠበቅ፣ የማስረጽና የማስቀጠል ኃላፊነት ለጥያቄ አይቀርብም ያሉት ፓትሪያርኩ በሰዎች መካከል አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ጠንክሮ የማስተማር፣ የመምከርና የማስታረቅ ኃላፊነት የእኛ ነው ብለዋል።
ከዚህም አንጻር የዘንድሮ ርክበ-ካህናት በተለይም ሰላም በማጽናትና ሌሎች ተልዕኮዎችን በመፈጸም ምን ያህል አሳክቷል የሚውለውን ጉዳይ በጥልቀት እንደሚመረመርና ቀጣይ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል።
በተጓዳኝም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተፈጥሮ በነበረው ጦርነት ውድመት የደረሰባቸውን አብያተ-ክርስቲያናት ወደ ነበሩበት አቋም ለመመለስ በሚያስችሉ ነጥቦች ላይም ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ቤተክርስቲያን ጸንታ የመቆሟ መሰረት ሰላም መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም የሕዝብን ደኅንነት ብሎም የአገርን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አስተላልፈዋል።