በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር የትግራይ ክልልን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ዝግጅት እያደረጉ ነው- የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር የትግራይ ክልልን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ዝግጅት እያደረጉ ነው- የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2015(ኢዜአ)፡-በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር የትግራይ ክልልን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶች ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገለጸ።
52ኛው ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ከግንቦት 8 -13 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ይካሄዳል።
በዚህ ውድድር ሁሉም ክልሎች የሚሳተፉ ሲሆን ትግራይ ክልልን ወክለው የሚወዳደሩ ከ50 በላይ አትሌቶች ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኪዳኔ ተክለሃይማኖት፤ ለውድድሩ እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ከሀገር አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች በኮቪድ 19 እና በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከሶስት ዓመት በላይ አትሌቶች ከውድድር መድረክ እርቀው ነበር ሲሉ አስታውሰዋል።
የተፈጠረውን ሰላም ተከትሎ ግን የክልሉ አትሌቶች ጠንካራ ልምምድ በማድረግ ለውድድር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው 52ኛው ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
የአትሌቶቹ ምርጫ በክልሉ የውስጥ ውድድር በማድረግ የተሻሉትን ከ50 በላይ አትሌቶች በመምረጥ የተከናወነ መሆኑን ገልጸው ለውድድሩ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
በሻምፒዮናው ከ100 ሜትር ጀምሮ እስከ 10 ሺህ ሜትር በሚደረጉ የተለያዩ ርቀቶች አትሌቶቹ የሚወዳደሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በፋይናንስ እጥረት ምክንያት አትሌቶቹ ያደረጉት ዝግጅት አጭር ጊዜ ቢሆንም በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ውጤት እንደሚያመጡ ያላቸውን እምነት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።
የክልሉ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ስፖርቱን ለማነቃቃት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው የስፖርቱ ባለድርሻ አካላትና በተለይም ባለሀብቶች በቀጣይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።