የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የሀላላ ኬላ የቱሪስት መዳረሻን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የሀላላ ኬላ የቱሪስት መዳረሻን ጎበኙ
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የኮይሻ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነውን የሀላላ ኬላ የቱሪስት መዳረሻ ጎበኙ።
የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በሀገረ-መንግሥት ግንባታና ህብረ ብሄራዊ አንድነት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ትናንት በአርባ ምንጭ ከተማ መጀመራቸው ይታወቃል።
ከውይይቱ በተጓዳኝም በአርባ ምንጭና አካባቢው የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን የመጎብኘት እቅድ ይዘዋል።
በዚህም መሰረት በዛሬው እለት የኮይሻ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካልና በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የሆነውን የሀላላ ኬላ የቱሪስት መዳረሻ ጎብኝተዋል።
የሀላላ ኬላ በዳውሮ ዞን የግልገል ጊቤ 3 ኃይል ማመንጫ ሰው ሰራሽ ኃይቅን ተንተርሶ የሚገኝ ድንቅ መልክዓ ምድር የተቸረው ስፍራ ነው።
ስፍራው ለቱሪስት መዳረሻ ይሆን ዘንድ በኮይሻ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ስር ታቅፎ ለቱሪስት መዳረሻነት በዘመናዊ መልኩ ተገንብቶ ለቱሪስቶች ክፍት ሆኗል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም ይህንኑ ስፍራ ተዘዋውረው መጎብኝት ችለዋል።
ከጉብኝቱ በኋላም ኢዜአ ያነጋገራቸው የፓርቲ አባላት፤ በገበታ ለሀገር እሴት ተጨምሮበት የለማው ሀላላ ኬላ ለአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚነት እና ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልፀዋል።
የሐላላ ኬላ ኢትዮጵያ ዕምቅ የተፈጥሮ ፀጋዎቿን በማልማት ከቱሪዝም ዘርፍ መጠቀም እንድትችል ጉልህ ማሳያ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።