ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ


አዲስ አበባ ግንቦት 2/2015(ኢዜአ):- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቢልዋል ቡቶ ዛርዳሪ ጋር በካራቺ ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ለማሻሻል ቁርጠኛ መሆኗን አምባሳደር ምስጋኑ ገልጸዋል።

የሁለቱን አገራት ግንኙነት በተለያዩ የትብብር ማዕቀፎች እንዲጠናከር እየተደረገ መሆኑንና የሁለትዮሽ ትብብሩን በቀጣናዊ የጋራ ጉዳዮችም ለማጎልበት እንደሚሰራ አመልክተዋል።


የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቢልዋል ቡቶ ዛርዳሪ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በአገራቱ መንግስታት አማካኝነት አበረታች ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።


የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካራቺ አዲስ የቀጥታ በረራ መጀመሩ ግንኙነታቸው እየተጠናከረ መምጣቱን ማሳያ ነው ብለዋል።


ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት በኢዝላማባድ ኤምባሲዋን መክፈቷ በአገራቱ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል ነው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።


ወደ ፓኪስታን በማምራት የዲፕሎማሲያዊ ስራዎች እያከናወነና በቢዝነስ ጉባኤዎች ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በካራቺ የነበረውን ቆይታ አጠናቆ ወደ ኢዝላማባድ ማምራቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም