ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ 23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ግንቦት 2/2015(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።

ኢትዮጵያ መድን ከሲዳማ ቡና ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ኢትዮጵያ መድን በ41 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን በአንጻሩ ሲዳማ ቡና በ24 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ኢትዮጵያ መድን በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ በሁለቱ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በሁለቱ ሲሸነፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን 4 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ23ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር ሃዋሳ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሃዋሳ ከተማና ሀዲያ ሆሳዕና በተመሳሳይ 31 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 8ኛ እና 7ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ሃዋሳ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለቱን ሲያሸንፍ በሶስቱ ሽንፈት ገጥሞታል።

ሀዲያ ሆሳዕና በበኩሉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ በተደረጉ ጨዋታዎች ባህር ዳር ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 3 ለ 1 እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 0 አሸንፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም