ቀጥታ፡

የገበሬዎች ኀብረት ሥራ ማኀበራትና አርሶ አደሮች ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች በቀጥታ ግብአት እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው - የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2015 (ኢዜአ) ፡-የገበሬዎች ኀብረት ሥራ ማኀብራትና አርሶ አደሮች ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች በቀጥታ ግብአት የሚያቀርቡበት የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ አገር አቀፍ ኤክስፖ እየተካሄደ ነው።  

በኤክስፖው ላይ ከ350 በላይ ባለኃብቶችና ኩባንያዎች እየተሳተፉ ሲሆን በአምራች ዘርፉ የተደረሰበትን ደረጃ የሚያሳዩ ኢንዱስትሪ ውጤቶች ቀርበዋል።   

ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት እየተደረገ ያለውን ጥረት፣የተገኙ ውጤቶችና ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችንም ማሳየት የኤክስፖው ሌላው ዓላማ ነው።  

ከኤክስፖው ጎን  ለጎንም የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ላይ ምን ችግሮች አሉ?እንዴት ይፈታሉ?፣ከማን ምን ይጠበቃል? በሚለው ዙሪያ የሚመክር የፓናል ውይይትም ተካሂዷል።   

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ ሀሰን መሀመድ፤ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ለኢንዱስትሪዎች የግብዓት እጥረት ፈተና መሆኑን ጠቅሰዋል።        

ለዚህ ደግሞ አንዱ ችግር የገበያ ትስስር በሚፈለገው ደረጃ አለመኖር አንዱ ምክንያት መሆኑን ጠቁመው እሴት የማይጨምሩ ደላላዎች የሚፈጥሩት ሰው ሰራሽ እጥረት ትልቅ ችግር መሆኑን አክለዋል።

የገበሬዎች ኀብረት ሥራ ማኀብራትና አርሶ አደሮች ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች በቀጥታ ግብአት የሚያቀርቡበት የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን ሚኒስትር ደኤታው ገልጸዋል።   

ከ144 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶችን ለሚያቀነባብሩ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንዲያቀርቡ ስልጠና ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል።   

40 የገበሬዎች ኀብረት ሥራ ማኀበራት ጋር ትስስር ተፈጥሮ ግብዓቶችን እንዲያቀርቡ እየተደረገ መሆኑም እንዲሁ።     

ከቆዳና ሌጦ አቅርቦት ጋር የተያያዘውን ችግር ለመፍታት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ባሉት ማዕከላት ቆዳና ሌጦ በመሰብሰብ ለኢንዱስትሪዎች እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወንድማገኝ ነገራ፤ ምርት ገበያው በተለይ ዘይት ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ልዩ መስኮት ከፍቶ አኩሪ አተር እያቀረበ ነው ብለዋል።  

ልዩ መስኮቱ ኢንዱስትሪዎች በሚፈልጉት መጠን እና ጥራት ግብዓት የሚሆናቸውን ምርት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሚያዚያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን ነገ እንደሚጠቃለል ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

 

  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም