ኢትዮጵያና ፓኪስታን የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር እየሰሩ ነው- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ፓኪስታን የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር እየሰሩ ነው- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2015(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያና ፓኪስታን የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ20 አመታት በኋላ ወደ ፓኪስታኗ ካራቺ ከተማ ዳግም በረራ ጀምሯል።
በዚሁ ጉዞ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ የተመራ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የቢዝነስ ልኡክ ፓኪስታን ተገኝቷል።
በካራቺ የሁለቱ ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም የተካሄደ ሲሆን በመድረኩም የዘርፉ ተዋናዮች በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዳግም ወደ ካራቺ በረራ መጀመሩ ለሁለቱ አገሮች ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት ያለቀ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በተለይም በኢንቨስትመንትና በንግድ የአገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያና ፓኪስታን የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲያቸውን ለማጠናከር እየሰሩ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ የወጪ ንግድን መጨመርና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኑንም አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስተዋወቅና አዳዲስ የኢኮኖሚ መስኮችን ለመክፈት የጋራ ፎረሙ የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።
ከፎረሙ በተጓዳኝ የአገራቱ የንግድ ምክር ቤቶች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት አድርገዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ በነገው እለት ወደ ኢስላማባድ በማቅናት አዲስ የተከፈተውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚመርቁ መሆኑን የኢዜአ ሪፖርተር ከስፍራው ዘግቧል።