በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተጀመሩ ትልልቅ ግቦችን ለማሳካት ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ድጋፍን ማጠናከር ይገባል -አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተጀመሩ ትልልቅ ግቦችን ለማሳካት ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ድጋፍን ማጠናከር ይገባል -አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2015(ኢዜአ)-በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተጀመሩ ትልልቅ ግቦችን ለማሳካት ምቹ ሁኔታ መፍጠርና ድጋፍን ማጠናከር እንደሚገባ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ታምርት አገራዊ ንቅናቄ የተጀመረበትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አደራሽ የንግድ ኤክስፖ እየተካሄደ ነው።
ኤክስፖው ከሚያዚያ 29 እስከ ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን በርካታ አምራች ድርጅቶች ምርቶቻቸውን አቅርበዋል።
በኤክስፖው ከ350 በላይ ባለኃብቶችና ኩባንያዎች እየተሳተፉ ሲሆን የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂ፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ አልባሳት እንዲሁም የተለያዩ የቆዳ ውጤቶች ቀርበዋል።
የኤክስፖው ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ምርት ምን ደረጃ ላይ ነው? ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን መተካት ሂደት የሚኖረው አስተዋጽኦ ለመገምገም ነው ተብሏል።
አምራቾችና ኀብረተሰቡ እንዲሁም ተረካቢዎች የገበያ ትስስር መፍጠር ሌላው የኤክስፖው ዓላማ መሆኑ ታውቋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ በኤክስፖው ላይ የቀረቡ ምርቶችን በስፍራው ተገኝተው ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ኢትዮጵያ በዘርፉ ትልቅ አቅም ያላት መሆኑን ያየንበት ነው ያሉት አቶ አደም ሌሎች ባለኃብቶችንም ወደ ዘርፉ ለመሳብ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ለአንድ ዓመት የዘለቀው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም ትልቅ ውጤት እየተገኘበት መሆኑንም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ልማት በኢኮኖሚው ላይ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መሰረት የሚጥል መሆኑንም ተናግረዋል።
ከሥራ እድል ፈጠራ፣ ከውጭ ምንዛሬ ግኝትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ ንቅናቄው አወንታዊ ውጤቶች እየተገኙበት መሆኑን አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ፤ አምራች ኢንዱስትሪው ልዩ ድጋፍ የሚሻ ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ልማት ለእድገት ካለው ወሳኝ ድርሻ ባለፈ ሰፊ የሰው ኃይል መያዝ የሚችል በመሆኑ ለዘርፉ እድገት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎችም በዛሬው እለት ኤክስፖውን ጎብኝተዋል።