በሐረሪ ክልል የኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት አገልግሎት ዛሬ ተጀምሯል--የክልሉ ንግድና ልማት ኤጀንሲ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል የኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት አገልግሎት ዛሬ ተጀምሯል--የክልሉ ንግድና ልማት ኤጀንሲ
ሐረር ግንቦት 1/2015(ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል የኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ሽያጭ ዛሬ መጀመሩን የክልሉ ንግድና ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የሐረሪ ክልል ንግድና ልማት ኤጀንሲ ሃላፊ አቶ ቡሽራ አሊዪ አገልግሎቱን ባስጀመሩበት ወቅት ለኢዜአ እንደገለፁት አገልግሎቱ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም የነዳጅ ማደያዎች ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
አገልግሎቱ ከመጀመሩ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ የሙከራ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸው አገልግሎቱን ከቴሌ ብር እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቱ የግብይት ስርዓቱን ፈጣን እና ቀልጣፋ ከማድረጉም በተጨማሪ የብር ንክኪን ለማስወገድ እና ለቁጥጥር አመቺ በመሆኑ ህገ ወጥነትን ለመከላከል ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል፡፡
ህገ-ወጥ የነዳጅ ንግድ ላይ ኤጀንሲው አስፈላጊውን ቁጥጥር ያደርጋል ያሉት ሃላፊው ማህበረሰቡም የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቱን እንዲጠቀም ጠይቀዋል፡፡
በሐረር ከተማ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆነው አሽከርካሪ ወጣት ናኦል አብረሃም “አገልግሎቱ መጀመሩ ጥሩ መሆኑን ጠቁሞ ከአገልግሎቱ ጎን ለጎን ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይት ላይ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት” ገልጿል፡፡
ሌላኛው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወጣት ከዲር ሲራጅ በበኩሉ ካሁን ቀደም በነበረው የነዳጅ ሽያጭ በተለይ ባለሶስት እግር ተሸከርካሪዎች ከሚቀዱት ነዳጅ ተጨማሪ ክፍያ ይጠየቁ እንደነበር በመጠቆም ሽያጩ በኤሌክትሮኒክስ ስርዓት እንዲሆን መደረጉ ችግሩን እንደሚቀርፈው ተናግሯል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ማእከላዊ ምስራቅ ሪጅን ሽያጭ ማናጀር አቶ ተስፋዬ አባተ በበኩላቸው መንግስት ከግንቦት ወር ጀምሮ የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ እንዲፈፀም ማወጁን ተከትሎ ተቋሙ አገልግሎቱን በተመለከተ የማስተዋወቅ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡
በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የኔትወርክ መቆራረጥ እንዳያጋጥም ቅድመ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንም አቶ ተስፋዬ ጠቁመዋል፡፡
በሐረሪ ክልል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4ተኛ ቅርንጫፍን በመወከል የተገኙት አቶ ሃብቱ ሞገስ በበኩላቸው የኤሌክትሮኒክስ ነዳጅ ግብይት አገልግሎቱን ለማሳለጥ በነዳጅ አፕ አግልግሎቱን እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በሐረር ከተማ የኖክ ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሞላ በበኩላቸው የኤሌኬትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት መጀመሩ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻሉን እና ቀደም ሲል ያጋጥሙ የነበሩ ችግርችን የሚቀንስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡