የመዲናዋን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ለማጽናት ከአካባቢያዊ፣ ከአገራዊ እና ከዓለም አቀፋዊ የልማት ስራዎች ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል - ሙዐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት - ኢዜአ አማርኛ
የመዲናዋን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ለማጽናት ከአካባቢያዊ፣ ከአገራዊ እና ከዓለም አቀፋዊ የልማት ስራዎች ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል - ሙዐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2023(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ለማጽናት ከአካባቢያዊ፣ ከአገራዊ እና ከዓለም አቀፋዊ የልማት ስራዎች ጋር ማጣጣም እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሙዐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ኦቪድ ግሩፕ ጋር በመተባበር "አዲስ አበባን በአዲስ የዲፕሎማሲ ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጁት የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የታሪክ ምሁራን፣ የኪነ-ጥበብ እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እንዲሁም ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሙዐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከተሞች የብዝሃነት መገለጫ ናቸው ያሉ ሲሆን አዲስ አበባም ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የአፍሪካውያንና የዓለም አቀፉ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ መቀመጫ በመሆኗ ለነዋሪዎቿ ምቹ ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
እንደ አዲስ አበባ የበርካታ ዜጎች መኖሪያ የሆኑ ከተሞችም አካባቢያዊ፣ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊነትን ባሰናሰለ መልኩ የከተማ ልማትን መተግበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመዲናዋ ያሉ ሆቴሎችና ተቋማትም ዓለም አቀፋዊነትን በመላበስ አገልግሎታቸውን የተሻለ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
የከተማዋን ውበትና ጸጥታ በማስጠበቅ ምቹና ተመራጭ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመወከል ንግግር ያደረጉት አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን፥ አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን፣ የአፍሪካውያን እና የዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ማዕከልነቷን አስጠብቃ እንድትቀጥል ተከታታይ የአመራር ትውልዶች ጥበብ የተሞላበት የዲፕሎማሲ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በመዲናዋ ግዙፍ እና ውጤታማ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፥ በቀጣይም አዲስ አበባ ሁሉንም ባቀፈ መልኩ ዕድገቷን እንድታስቀጥል በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በመዲናዋ የተከናወኑት የወዳጅነት አደባባይ፣ የአንድነት እና የእንጦጦ ፖርኮች የከተማዋን እድገት በማፋጠን ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ አዲስ አበባ ከተማን ከዲፕሎማሲ፣ ከመሰረተ ልማት፣ ከመገናኛ ብዙኃን፣ ከለውጥ ስራዎችና ቀጣይ አቅጣጫን መሰረት ያደረጉ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር እየተደረገባቸው ይገኛል።