የኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የቢዝነስ ፎረም በፓኪስታን ካራቺ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የቢዝነስ ፎረም በፓኪስታን ካራቺ ተጀመረ
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2015(ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ እና ፓኪስታን የቢዝነስ ፎረም በፓኪስታን ካራቺ ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።
ፎረሙ ሁለቱ ሀገራት በንግድ እና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ግንኙነት በሚያጠናክሩባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ እየመከረ ይገኛል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊና የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች።
ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እያደረገች መሆኑን ጠቅሰው የፓኪስታን ባለሃብቶች እድሉን እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል።
የፓኪስታን ንግድ ልማት ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈጻሚ ዙቤር ሞቲዋላ በበኩላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካራቺ የሚያደርገውን በረራ መጀመሩ ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ባሻገር ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታጠናክር ዕድል ይፈጥርላታል ብለዋል።
ፓኪስታን ከአፍሪካ ጋር ባላት ግንኙነት ኢትዮጵያ ቁልፍ አገር ናት፤ አገራቱ ያላቸውን እምቅና ተነጻጻሪ የቢዝነስ አቅም በመጠቀም የንግድ ልውውጣቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር የኢትዮጵያ መንግስት ከፓኪስታን ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በፎረሙ መክፈቻ ላይ በኢትዮጵያ ስላለው የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ አማራጮችና ምቹ ሁኔታዎች ላይ ገለጻና ውይይት ተደርጓል።
በፎረሙ ላይ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የመንግሥት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከ60 በላይ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በቆይታው ሁለቱ አገራት በቱሪዝምና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የመግባቢያ ሥምምነት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያና ፓኪስታን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 64 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2022 ኤምባሲዋን በኢስላማባድ መክፈቷ ይታወሳል።
የሁለቱ አገራት ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ ከ7 እስከ 8 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አገራቱ ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ መጠኑን ወደ 300 ሚሊዮን ዶላር ለማድረስ የሚያስችላቸውን ተግባራት በማከናወን ላይ ይገኛሉ።
ከ80 በላይ የፓኪስታን ባለሀብቶችን ያቀፈ የንግድ ልዑክ በየካቲት 2015 ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የኢንቨስትመንት አማራጮችን መመልከቱ የሚታወስ ነው።