ቀጥታ፡

በመዲናዋ የተከናወኑ ግዙፍ የልማት ስራዎች የከተማዋን እድገት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ግንቦት 1/2015(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የተከናወኑት የወዳጅነት፣ የአንድነት እና የእንጦጦ ፓርኮች ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ የልማት ስራዎች የከተማዋን እድገት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና አቪድ ግሩፕ ጋር በመተባበር "አዲስ አበባን በአዲስ የዲፕሎማሲ ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።


 

በምክክር መድረኩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም፣ የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ፤ እንዲሁም ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የታሪክ ምሁራን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ ዲፕሎማቶች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንንን በመወከል መልእክቱን ያስተላለፉት አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን ናቸው።

በመልዕክታቸውም አዲስ አበባ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የአፍሪካውያን እና የሌሎች ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ማዕከልነቷን አስጠብቃ እንድትቀጥል ተከታታይ የአመራር ትውልዶች ጥበብ የተሞላበት የዲፕሎማሲ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በመዲናዋ ያሉ መንገዶች በአፍሪካ አገራት መሰየማቸውን ጨምሮ የቪዛ አገልግሎት እና ሌሎች ጉዳዮች እየተሻሻሉ መምጣታቸው የሚመሰገኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመዲናዋ ግዙፍ እና ውጤታማ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመው፥ በቀጣይም መዲናዋ ዕድገቷን እንድታስቀጥል በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የወዳጅነት አደባባይ፣ የአንድነት እና የእንጦጦ ፓርኮች የከተማዋን ጥራት በማስጠበቅ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው እንደሆኑም ገልጸዋል።

በቀጣይም የመዲናዋን እድገትና ገጽታ የሚያስጠብቁ የልማት ስራዎች በተጨማሪ የበጎ ፈቃድ እና የስራ እድል ፈጠራን በማስፋት ሰው ተኮርን ማዕከል ያደረጉ የልማት ስራዎች ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ከተሞች የኮንፍረንስ ቱሪዝም ማዕከል አድርገው ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ጠቅሰዋል።

በዚህም የአዲስ አበባን ተመራጭነት ለማጎልበት የጸጥታ፣ የመሰረተ ልማት፣ የአገልግሎት፣ የእንግዳ ተቀባይነት እና ሌሎች ህብረተሰቡን ያሳተፈ ተወዳዳሪነትን ማጎልበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፥ ከተሞችን በአካባቢያዊ፣ በአገራዊና ዓለም አቀፋዊ መሰረቶች ታሳቢ ያደረገ ልማትን ማስቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማንም ከሌሎች አካባቢዎች ጋር አጣጥሞ በማልማት አካባቢያዊ፣ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ መሰረቶችን መሰረት በማድረግ ለኢትዮጵያውያን እና ለዓለም አቀፉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ምቹ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላችው ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሚለውን አገራዊ መርህ በመከተል ኢዜአ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቀጣይም የመረጃ ተደራሽነቱን ለማስፋት ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በመገንባት በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በመድረኩ ላይ የተለያዩ የመነሻ ጹህፎች ቀርበው ምክክር ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም