በኦሮሚያ ክልል ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ተጀመረ
አዳማ ግንቦት 1 / 2015 (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ዛሬ በሁሉም የነዳጅ ማደያዎች በይፋ ተጀምሯል ።
የነዳጅ ግብይቱ የሚከናወነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ና በሌሎችም መተግበሪያዎች እንደሆነ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ደረጀ ፉፋ የነዳጅ ግብይቱ በኤሌክትሮኒክስ መሆኑ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ሀብት ለታለመለት ዓላማ በማዋል ረገድ ያለው ፋይዳ ጉልህ መሆኑን ገልጸዋል።
ዲጂታል የነዳጅ ግብይት አገልግሎቱ በሞባይል ባንኪንግና መተግበሪያው አማካኝነት ከአንድ ሺህ ማደያዎች በላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ጎሹ በበኩላቸው ዛሬ በክልሉ የተጀመረው ዲጂታል የነዳጅ ግብይት አገልግሎት ነዳጅ ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ በአግባቡ እንዲደርስ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ግብይቱ ቅሸባ፣ሌብነትና ማጭበርበር በማስቀረት ሀብቱ ለታለመለት ዓላማ በማዋል ረገድ ያለው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
የዲጂታል ነዳጅ ግብይት አገልግሎት ተጠቃሚዎች በበኩላቸው አገልግሎቱ በዲጂታል መሆኑ ነዳጅ ለመቅዳት የሚደረገውን ረዥም ሰልፍ እንደሚያስቀር ገልጸዋል።
ይሁንና ግብይቱ የተፋጠነ እንዲሆን የኔትወርክ አገልግሎት የተሳለጠ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።