የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ እያካሄዱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ እያካሄዱ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 1/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እያካሄዱ ነው።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ፤ የምክክር መድረኩን ዋነኛ ትኩረትና ዓላማውን በማስመልከት ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የምክክር መድረኩ በተለይም በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ላይ በማተኮር ለአንድ ሳምንት ይካሄዳል ብለዋል።
በመድረኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በዚሁ ዙሪያ ሰፊ ውይይት የሚያደርጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምና ልማትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ውይይት ለቀጣይ ሀገራዊ የምክክር መድረኮች በጽንሰ-ሀሳብ ደረጃ መቀራረብ ለመፍጠርም ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የስትራቴጂክ ዕቅድ አዘገጃጀት ዙሪያም በባለሙያዎች ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ዶክተር መብራቱ ጠቁመዋል።
የጋራ ምክር ቤት አባላቱ ከጉባዔው ጎን ለጎን በአርባ ምንጭ ከተማና ሌሎችም አካባቢዎች የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።