ቀጥታ፡

ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው


አዲስ አበባ ግንቦት 1/2015(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23 ሳምንት መርሐ-ግብር የሁለተኛ ቀን ውሎ ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ሁለቱ ክለቦች ጨዋታቸውን ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ያደርጋሉ።

በደረጃ ሰንጠረዡ ባህር ዳር ከተማ በ44 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና በ31 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ባህር ዳር ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በሶስቱ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል።

ባህር ዳር ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን እስኪያደርግ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ዝቅ ማድረግ ይችላል።

በአንጻሩ ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታውን ካሸነፈ ከነበረበት 6ኛ ደረጃ ወደ 4ኛ ከፍ ይላል።
የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ለጨዋታው ተጨማሪ ድምቀት ይሰጡታል ተብሎ ይጠበቃል።

ፌደራል አርቢትር ቢኒያም ወርቅአገኘሁ የሁለቱን ክለቦች ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ 3 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ሌላኛው የ23ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከድሬዳዋ ከተማ ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ያገናኛል።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ11 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ በ27 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም፤ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል በሶስቱ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ 2 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና ትናንት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ በተደረጉ ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ ከአዳማ ከተማ እንዲሁም ፋሲል ከነማ ከአርባ ምንጭ ከተማ በተመሳሳይ አንድ አቻ ተለያይተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም