አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የብድር አገልግሎት እንዲጨምር አድርጓል - የብሔራዊ ባንክ ገዥ - ኢዜአ አማርኛ
አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የብድር አገልግሎት እንዲጨምር አድርጓል - የብሔራዊ ባንክ ገዥ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2015(ኢዜአ)፦ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የብድር አገልግሎት እንዲጨምር አድርጓል ሲሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።
ይህም ምርታማነትን በማሳደግ በምጣኔ ሃብት እድገት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ አስችሏል ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የ2015 የፋይናንስ ተደራሽነት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይም በብድር አቅርቦት ላይ ጥሩ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
በተለይም አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የብድር አገልግሎት እንዲጨምር በማድረጉ የግሉ ዘርፍ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በመሆኑንም መንግሥት የግሉን ዘርፍ በዘላቂነት ለመደገፍ ከግል ባንኮች በተጨማሪ የልማት ባንክ ሰፋ ያለ የብድር አገልግሎት እንዲያቀርብ መደረጉ አንዱ የፖሊሲ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ለአምራች ኢንዱስትሪው ምርታማነት እንቅፋት የሆነውን የውጪ ምንዛሬ ችግር ለመፍታት በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተወሰደው እርምጃ ቅድሚያ እንዲያገኝ መደረጉን ተናግረዋል።
በዚህም አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለግሉ ዘርፍ የሚሰጠውን የብድር አገልግሎት በመጨመር ምርታማነትን በማሳደግ በምጣኔ ሃብት እድገት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ ማስቻሉን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው መንግሥት ባለፉት ሦስት ዓመታት በወሰደው የፖሊሲ እርምጃዎች ለግሉ ዘርፍ ምቹ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖር ማስቻሉን ተናግረዋል።
በዚህም የግሉ ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረው ይህ በምጣኔ ሀብት እድገቱ ላይ የራሱ የሆነ ድርሻና አስተዋፆኦ እንዳለው አክለዋል።