የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ20 አመታት በኋላ ዳግም ወደ ፓኪስታኗ ከተማ ካራቺ በረራ ዛሬ ማምሻውን አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ20 አመታት በኋላ ዳግም ወደ ፓኪስታኗ ከተማ ካራቺ በረራ ዛሬ ማምሻውን አስጀመረ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ20 አመታት በኋላ ዳግም ወደ ፓኪስታኗ የንግድ ከተማ ካራቺ በረራ ዛሬ ማምሻውን አስጀመረ።
አየር መንገዱ በመጀመሪያ በረራው የንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ ያቀፈ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ይዞ ነው ወደ ሥፍራው ያቀናው።
የልዑክ ቡድኑ በቆይታው ሁለቱ አገራት በቱሪዝምና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የመግባቢያ ሥምምነት እንደሚያደርግ ይጠበቃል ተብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ ለማ ያዴቻ በጉዞው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እንደገለጹት በረራው መጀመሩ የአገራቱን ኢኮኖሚያዊ አጋርነት ያጠናክረዋል።
በተለይም የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስርን ለማጠናከርና የቱሪዝም ፍሰትን ለማጠናከር እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሾዛብ አባስ በበኩላቸው በረራው እንዲጀመር በሁለቱ አገራት መካከል ሲደረግ የነበረው ጥረት ፍሬ አፍርቶ በረራው ዛሬ በመጀመሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።
በረራው መጀመሩ የሁለቱን አገራት የዲፕሎማሲው ግንኙነት በተለይም ደግሞ የኢኮኖሚ ትስስሩን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው ጠቁመዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው ምስጋኑ አርጋ የሚመራ ልዑክ ቡድን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተውጣጡ አባላትን የያዘ ነው ተብሏል።
አየር መንገዱ ወደ ካራቺ የጀመረው በረራ በሳምንት አራት ጊዜ የሚያደርግ ሲሆን አየር መንገዱ በእስያ የሚያደርገው በረራ ወደ 37ኛው መዳረሻ ከፍ ያደርገዋል።