ከአቬዬሽን ዘርፍ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው - ዶክተር አለሙ ስሜ - ኢዜአ አማርኛ
ከአቬዬሽን ዘርፍ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው - ዶክተር አለሙ ስሜ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2015(ኢዜአ): ኢትዮጵያ ከአቬዬሽን ዘርፍ የምታገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ።
የአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር 11ኛውን የአየር ትራንስፖርት ባለድርሻ አካላት የሁለት ቀናት ውይይት በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዶክተር አለሙ ስሜ የአቬሽን ኢንዱስትሪው ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ለኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ዘርፍ ነው ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ መንግሥት የአየር ትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከዚህም አንጻር በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራቸው የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፣ የአየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ የተሳለጠ በማድረግ የአፍሪካዊያንን ግንኙነት ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ በመመራት በራሱ ጥረት ለአህጉሪቷ የአቬሽን ኢንዱስትሪ መነቃቃት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም የበረራ መዳረሻውን በማስፋት ለአፍሪካዊያን የአየር ትራንስፖርት መሻሻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር ዋና ጸኃፊ አብደራሀማን በርቴ ማህበሩ የአፍሪካዊያን የአየር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ምቹ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ አባል አገራትም አፍሪካዊያን ምቹ የአየር የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሥርዓት በመዘርጋት በትብብር መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።