በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ለሚደረገው የኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት በቂ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከነገ ጀምሮ ተግባራዊ ለሚደረገው የኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት በቂ ዝግጅት ተደርጓል
ሚዛን አማን ሚያዝያ 30 / 2015 (ኢዜአ) በክልሉ ከነገ ጀምሮ ለሚተገበረው የኤሌክትሮኒክስ የነዳጅ ግብይት ሥርዓት በቂ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው ለዲጂታል ክፍያ ሥርዓት አፈጻጸም ስኬታማነት ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቋል።
የቢሮው ምክትልና የንግድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አምዴ ፋሪስ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ከነገ ግንቦት 01 ቀን 2015ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ባሉት ማደያዎች የነዳጅ ምርቶች ግብይት ከኤሌክትሮኒክስ ግብይት ውጭ አይፈጸምም።
በዚህ መሠረት በስድስት ዞኖች ውስጥ የሚገኙ 24 የነዳጅ ማደያዎች ለተሽከርካሪዎች ነዳጅ ሲቀዱ ግብይቱን በዲጂታል አገልግሎት ብቻ እንዲፈጽሙ የሚያስችል ግንዛቤ መፈጠሩን ተናግረዋል።
በቅድመ ዝግጅት ሥራው ማደያዎች የጄኔሬተርና የዋይ ፋይ(Wi-fi) ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲያሟሉ መደረጉን አቶ አምዴ ጨምረው አስታውቀዋል።
ከዚህ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥርዓት ውጭ ለመንቀሳቀስ የሚሞክሩና ግብይቱን ተግባራዊ የማያደርጉ ማደያዎች ደግሞ በቀጥታ ከገበያ እንዲወጡ ይደረጋል ብለዋል።
ቢሮው ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት የግብይቱን ትግበራ የሚከታተል የጋራ ግብረ ኃይል በሁሉም ዞኖች አዋቅሮ አፈጻጸሙን ለመከታተል መሰማራቱንም ገልጸዋል።
ለአፈጻጸሙ ስኬት ድርሻ ያላቸው የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ፣ ባንኮችና ኢትዮ-ቴሌኮም የጋራ ግንዛቤ በመያዝ ከቢሮው ጋር በመሆን የድርሻቸውን ለመወጣት እንደተሰማሩም አቶ አምዴ አመልክተዋል።
በቅድመ ዝግጅት ሥራ በነዳጅ ማደያዎች ውስጥ ለሚሰሩ ኦፕሬተሮች ሥልጠና የተሰጠ ሲሆን፣ ለተሽከርካሪ ባለንብረቶችም በግብይቱ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲጨብጡ መደረጉን ተናግረዋል።
በትግበራው ወቅት ሊታዩ የሚችሉ ዘመናዊ የክፍያ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግሮችን በድጋፍና ክትትል በማረም ተግባሩን ለማቀላጠፍ እንደሚሰራም አስረድተዋል።
አዲሱ የነዳጅ ግብይት ሥርዓት እንደ ሀገር ለነዳጅ እየወጣ ያለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለታለመለት አላማ በአግባቡ እንዲውል የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም የሚመለካታቸው አካላት አፈጻጸሙን እንዲደግፉም ጠይቀዋል።