ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዳግም ወደ ካራቺ በረራ መጀመሩ የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናክራል - አምባሳደር ጀማል በከር

አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዳግም ወደ ፓኪስታን ካራቺ በረራ መጀመሩ የሁለቱን አገራት ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክር በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ገለጹ። 

ካራቺ ለአየር መንገዱ 37ኛ የእስያ መዳረሻ እንደሆነች ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ካራቺ ከተማ ከ20 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በረራ የሚጀምር ሲሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ምስጋኑ አርጋ የሚመራ ከፍተኛ የመንግሥት ልዑካን ቡድን ወደ ስፍራው ያቀናል። 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚመራው ልዑክ ቡድን ውስጥ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተውጣጡ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ተካተዋል።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኤምባሲና የፓኪስታን ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ ወደ ፓኪስታን ካራቺ የሚያመራውን ልዑክ ለመቀበል ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ተገልጿል።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ጉዞውን አስመልክቶ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ የፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤን ይዞ ኢትዮጵያን በዓለም እያስተዋወቀ ነው።


 

አየር መንገዱ ከረዥም ዓመታት በኋላ ዛሬ ማምሻውን ወደ ፓኪስታኗ የንግድ ከተማ ካራቺ ዳግም በረራ መጀመሩ የሁለቱን አገራት አጋርነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።  

በተለይም የሁለቱ አገራት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርም ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ በቱሪዝም መስክ እያደረገች ያለውን የለውጥ ስራዎች ከዳር ለማድረስም የበረራው መጀመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው አምባሳደር ጀማል ያመለከቱት።

በፖለቲካው መስክም የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ለማጠናከር እንዲሁም ሁለቱ አገራት ተቀራርበው በመስራት የጋራ ጥቅሞችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የበረራው መጀመር የራሱ አበርክቶ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በረራው አፍሪካን ከፓኪስታንና ከተቀረው የደቡብ እስያ አካባቢዎች ጋር በኢኮኖሚ ይበልጥ ለማስተሳሰርና ለማጠናከር እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ፓኪስታን ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ የኢንቨስትመንት መዋዕለ-ንዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት እያሳየች መሆኑን በማንሳት ለዚህም ስኬት በረራው መጀመሩ የሚኖረው ድርሻ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራው የልዑካን ቡድን በፓኪስታን በሚኖረው ቆይታ በካራቺና ኢስላማባድ በኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ መስክ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።  

አየር መንገዱ በረራው ከተጀመረ በኋላ በሳምንት አራት ቀናት ወደ ስፍራው በረራ እንደሚኖረው ተገልጿል። 

ካራቺ አየር መንገዱ 37ኛ የእስያ መዳረሻ ሲሆን ከዚህ ቀደም በኢስላማባድ መደበኛ የተጓዦች በረራ እያደረገ እንደሚገኝ ተጠቁሟል። 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ130 በላይ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች እንዳሉት አስታውቋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም