የመኸር ወቅት የግብርና ሥራዎችን የተሳካ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው - ክልሎች - ኢዜአ አማርኛ
የመኸር ወቅት የግብርና ሥራዎችን የተሳካ ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው - ክልሎች
አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2015(ኢዜአ)፦ የመኸር ወቅት የግብርና ሥራዎችን የተሳካ ለማድረግና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የተለያዩ ክልሎች ገለጹ።
የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን ክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ትኩረት አድርጓል ብለዋል።
በዘንድሮ የመኸር ወቅት የሚገኘውን ምርት ለመጨመር ትኩረት መደረጉን ጠቁመው ለዚህም ለእርሻ ምቹ የሆኑ አካባቢዎች ላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በዋናነትም የመሬት ዝግጅት፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የሰው ኃይል ዝግጅትና መሰል ተግባራት ላይ ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድርና የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪ፤ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ በበኩላቸው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በአርሶ አደሩ ከሚከናወን የግብርና ሥራ በተጨማሪ በግብርናው ዘርፍ የባለሃብቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ዘመናዊ የግብርና ሥራ ማጠናከር ላይ ትኩረት መሰጠቱን ነው የጠቆሙት።
ለዚህም መንግሥት በልዩ ሁኔታ የማዳበሪያ ድጎማ ማድረጉን ገልጸው በዘንድሮው የመኸር ወቅት ክልሉ የተሻለ ምርት ለማምረት ዝግጁ ነው ብለዋል።
በክልሉ የመኸር ወቅትን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ያሉት ደግሞ የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ሚስራ አብደላ ናቸው።
የበልግ ዝናብ ለመኸር ዝግጅቱ የላቀ አስተዋጽዖ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመው በዚህም በመኸር ወቅት እርሻ የሚካሄድባቸውን አካባቢዎች ከወዲሁ በአጫጭር ጊዜ ሰብሎች በመሸፈን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማጎልበት ላይ አበረታች ውጤቶች መመዝገቡን ተናግረዋል።
ለዚህም አመራሩ፣ ሙያተኛውና አርሶ አደሩ እየተናበበ የሚሰራበትን አሰራር ለመዘርጋት በየወረዳው ኮሚቴ በማዋቀር አርሶ አደሩ ድጋፍና ክትትል የሚያገኝበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም በክልሉ የምርትና ምርታማነትን አቅም ለማሳደግ በግብዓትና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑንም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ አስረድተዋል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ፋጆ ሳፒ ክልሉ ምርት አብቃይ ከሚባሉ የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል እንደሚጠቀስ ገልጸው ይህን አቅም ይበልጥ ማሳደግና ማበልጸግ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ክልሉ አርብቶና አርሶ አደር በብዛት ያለበት በመሆኑ በሁለቱም መስኮች ስኬታማ ሥራ ለማከናወን ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በተለይም የመኸር ወቅትን በክልሉ ከሚመረቱ ምርቶች በተጨማሪ አዳዲስ ዝርያዎችን ለመሞከር በሚያስችል መልኩ አርሶ አደሩን ማሰልጠንና ሙያተኞችን መመደብ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።