የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ በትኩረት መስራት አለበት-ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ በትኩረት መስራት አለበት-ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2015(ኢዜአ): የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸም ላይ ተወያይቷል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ባቀረቡት የአፈጻጸም ሪፖርት፤ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እምቅ ሀብቶችን የማስተዋወቅ ስራ በስፋት ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት 4 ነጥብ 55 ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዶ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሳብ መቻሉን ገልጸው፤ እቅዱን ማሳካት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።
ዘንድሮ የተገኘው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10 በመቶ ብልጫ ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም 168 የሚሆኑ አዲስ የውጭ እና የሀገር ውስጥ በለሀብቶች በተለያዩ መስኮች ላይ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እንዲያገኙ መደረጉን ገልፀው በቀጣይ ወራትም ሌሎች ባለሀብቶች ፈቃድ እንዲያገኙ ይደረጋል ነው ያሉት።
በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለ138 ሺህ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ55 ሺህ 436 ዜጎች ብቻ የስራ ድል መፈጠሩን አክለዋል።
ለእቅዱ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በመሆናቸው በቀሪ ወራት ክፍተቶችን ለማረም እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አሻ ያህያ፤ ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ዝቅትኛ አፈጻጸም ማሳየቱን ጠቅሰው፤ በቀሪ ወራት እቅዱን ለማሳካት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል።
ለዚህም በሀገሪቱ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን መጠቀምና ማስፋፋት እንደሚገባው ነው ያነሱት።
ኢንቨስትመንት ሊደረግባቸው የሚገባቸውን ዘርፎች ለይቶ በማስተዋወቅ የሀገሪቱን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲያድግ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሀገሪቱ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ልታገኝ የምትችለውን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ባለሀብቶች የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች እንዲፈቱ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ቋሚ ኮሚቴውም የበኩሉን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሀገሪቱ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታዎች ቢኖሩም በባለሀብቶች የሚነሱ የውጭ ምንዛሬ፣ የመሬትና መሰል ችግርችን አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ በምላሻቸው፤ በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ለማሳደግ የተቋማትን እና የክልሎችን ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ በቅንጅት መስራታችንን እናጠናክራለን ነው ያሉት።
በሀገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት በኢንቨስትመንት ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚቃኝ የመስክ ምልከታ መደረጉን አንስተው፤ በመልሶ ግንባታ ወደ ሙሉ የማምረት አቅማቸው እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።