ቀጥታ፡

ሐረርን በተቀናጀ እቅድ በመምራት ልማትና እድገቷን ለማፋጠን በቁርጠኝነት መስራት ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ


ሐረር ሚያዝያ 30/2015(ኢዜአ)፦ የሐረር ከተማን በተቀናጀ እቅድ በመምራት ልማትና እድገቷን ለማፋጠን በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል ሲሉ  የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስገነዘቡ።


ከተማዋን በተቀናጀ እቅድ ለመምራት የሚያስችል ክልላዊ ግብረ ኃይል ዛሬ ተቋቁሟል።


ግብረ ኃይሉ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን እንዲሁም የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮና የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤትን ያቀፈ መሆኑ ተመላክቷል።


 


የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ከግብረ ኃይሉ ጋር ባደረጉት ውይይት እንደገለጹት የሐረር ከተማን ልማትና እደገት ለማፋጠን በተቀናጀ እቅድ መምራትና መስራት ይገባል።


በከተማዋ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት፣ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ፣ ፅዳትና ውበቷን ለመጠበቅና የስራ እድል ለመፍጠር ተቋማት በተቀናጀ እቅድ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


በተለይም ሕገ ወጥ ግንባታና የመሬት ወረራ ላይ የተጀመረው የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራን በተቀናጀ አግባብ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።


ለተግባራዊነቱ አመራሩ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣና በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


"መሬትን ለከተማዋ እድገት መጠቀም ላይ ትኩረት ማድረግ  ያስፈልጋል" ሲሉም አክለዋል።


በክልሉ የተመሰረቱ የገጠር ከተሞችም የኢኮኖሚ ማዕከል ሆነው ለወጣቱ ሥራ እንዲፈጥሩ በማድረግ ረገድ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 


ግብረ ኃይሉ የከተማዋን ልማትና እድገት ለማፋጠን የሚያስችል የተቀናጀ እቅድ በማዘጋጀት ከወዲሁ ወደ ሥራ መግባት እንደሚገባው ርእሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል። 


በውይይቱ ላይ በግብረ ሀይሉ የታቀፉ የተቋማት አመራሮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም