በኃይል ልማት ዘርፍ የግሉን ሴክተር ተሳትፎ የሚያሳድጉ የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተዋል - ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ - ኢዜአ አማርኛ
በኃይል ልማት ዘርፍ የግሉን ሴክተር ተሳትፎ የሚያሳድጉ የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተዋል - ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2015(ኢዜአ):- በኃይል ልማት ዘርፍ የግሉን ሴክተር ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች መዘጋጀታቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።
የግሉ ዘርፍ በታዳሽ ኃይል ልማት ያለውን የአቅርቦት ክፍተት የመሙላት አቅም አለው ብለዋል።
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ስራ ላይ የነበረውን የኢነርጂ ፖሊሲ ከመከለስ ጀምሮ የዘርፉን ልማት የሚያጠናክሩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ገልጸዋል።
የግልና የመንግስት አጋርነት አዋጅ ጸድቆ ወደ ስራ መግባቱንና ይህም መሆኑ መንግስትና የግሉ ሴከተር በኃይል ልማት በትብብር እንዲሰሩ በማድረግ ላይ ነው ብለዋል።
የኢንቨስትመንት አዋጅ መሻሻሉም የአገር ውስጥና ከአገር ውጪ ያሉ ኢንቨስተሮች በኢነርጂ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ አመልክተዋል።
የግሉን ዘርፍ በኃይል ልማት ዘርፍ ለማሳተፍ የሚያስችል የፖሊስ ማዕቀፍ መዘጋጀቱንና በዚሁ ስር የመንግስትና የግሉ ዘርፍ በዘርፉ በጋራ መስራት የሚያስችላቸው መመሪያ መጽደቁንም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።
በሂደት ላይ የሚገኘው የፓወር ሴክተር ሪፎርም መመሪያ ተግባራዊ በሚደረግበት ወቅትም በኃይል ኢንቨስትመንት ተጨማሪ እድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት እምቅ ሃብት ቢኖራትም አቅርቦቱ እስካሁን ከ50 በመቶ በታች መሆኑንና የግሉ ዘርፍ በልማቱ ቢሰማራ የአቅርቦቱን ክፍተት መሙላት እንደሚችል ገልጸዋል።
የፖሊሲና የቁጥጥር ማዕቀፎች ላይ ማሻሻያ መደረጉ ለኢነርጂው ዘርፍ እድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
በተያያዘም በኃይል ልማት ዘርፍ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው ስራ ቀጣናዊ የልማት ትስስርን የሚያሳልጥና የኢትዮጵያን ተደማጭነት የመጨመር አቅም እንዳለውም ነው የገለጹት።
የኃይል ልማት ስራዎች ተጠናቀው ተደራሽ እስከሚሆኑ ድረስ ሕብረተሰቡ በአካባቢው በሚቀርቡለት አማራጮች የመጠቀም ልምዱን እንዲያሳድግ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።