በማረሚያ ቤቶች የህግ ታራሚዎች የሰብአዊ መብት አያያዝ ትርጉም ያለው ለውጥ አምጥቷል- የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በማረሚያ ቤቶች የህግ ታራሚዎች የሰብአዊ መብት አያያዝ ትርጉም ያለው ለውጥ አምጥቷል- የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን
አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2015(ኢዜአ): በማረሚያ ቤቶች የህግ ታራሚዎች የሰብአዊ መብት አያያዝ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ገለጹ፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮሚሽኑን የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የተቋሙን የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አባላት አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም ቀደም ሲል በማረሚያ ቤቶች የነበረው የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግር ከለውጡ በኋላ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
በማረሚያ ቤቶች በምናደርጋቸው ምልከታዎች ከቦታ ቦታ ልዩነቶች ያሉት ቢሆንም አጠቃላይ ሲታይ ግን አበረታች ለውጥ መኖሩን ጠቅሰው በቀጣይም ይበልጥ መሻሻል ያስፈልገዋል ብለዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ለሚገኙ ወገኖች አስቸኳይ እርዳታ ከማድረስ አኳያ መልካም እንቅስቃሴ መኖሩን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶችን በመከላከልና ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት ረገድም መሻሻሎች አሉ ብለዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋምና የወንጀል ተሳታፊዎችን ተጠያቂ በማድረግ በኩል ግን ክፍተቶች አሉ ነው ያሉት።
በመሆኑም መንግስት የሽግግር ፍትህን ተግባራዊ በማድረግ እርቅና ተጠያቂነትን ለማስፈን የጀመረው ጥረት መልካም ጅምር መሆኑን ገልጸዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቱ አለነ፤ ኮሚሽኑ ለሰብአዊ መብቶች መከበር እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም በዚህ ዙሪያ የተጠናከሩ ስራዎች መከናወን እንዳለበት አስገንዝበው በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የዜጎች ግንዛቤ እንዲዳብር ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የኮሚሽኑን ቅርንጫፎች በማስፋት በሰብአዊ መብቶች መከበር ዙሪያ የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀው ለዚህም ቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።