የካፒታል ገበያ ሲተገበር በኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ነው- ሳንዲ ራይት - ኢዜአ አማርኛ
የካፒታል ገበያ ሲተገበር በኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ነው- ሳንዲ ራይት
አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2015(ኢዜአ):- የካፒታል ገበያ ሲተገበር በኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን የቻርተርድ ኢንስቲትዩት ፎር ሴኪዩሪቲስ ኤንድ ኢንቨስትመንት ኤክስፐርት ሳንዲ ራይት ገለጹ።
መቀመጫውን ለንደን ያደረገው የተለያዩ አገራት የካፒታል ገበያዎች ላይ የባለሙያዎች ስልጠናና የአቅም ማጎልበቻ ድጋፍ የሚሰጠው 'ቻርተርድ ኢንስቲትዩት ፎር ሴኪዩሪቲስ ኤንድ ኢንቨስትመንት' ከኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ጋርም በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።
የካፒታል ገበያ አክሲዮን፣ ቦንድ፣ ተዛማጅ ውሎች የመሳሰሉ ሰነደ መዋዕለ ንዋዮች ግብይት የሚከናወንበት ቦታ ነው።
ባደጉት አገራት በስፋት የሚታወቀውን የካፒታል ገበያን በኢትዮጵያ ወደ ስራ ለማስገባት አዋጅ 1248/2013 ጸድቆና የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ተቋቁሞ በሂደት ላይ ይገኛል።
የ'ቻርተርድ ኢንስቲትዩት ፎር ሴኪዩሪቲስ ኤንድ ኢንቨስትመንት' ባለሙያ ሳንዲ ራይት፤ ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ለመጀመር እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀዋል።
"ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ለመጀመር እያደረገች ያለችው ዝግጅት ሌሎች ልምድ ካላቸው አገራት ጋር እኩል ደረጃ ላይ ሊያስቀምጣት የሚችል ነው ብለዋል።"
የካፒታል ገበያ በተለይም በቅርቡ የሚተገበረው የኢትዮጵያ ሰነድ መዋዕለ ንዋዮች ገበያ ጋር ተዳምሮ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ከውጭ የሚመጣ የገንዘብ አቅምን በማጠናከርና ቁጠባን በማሳደግ ረገድ ወሳኝ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።
በመሆኑም የካፒታል ገበያ ወደ ስራ ሲገባ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት ትልቅ ለውጥ ያመጣል ነው ያሉት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ስራ ኮሌጅ የአካውንቲንግና ፋይናስ መምህርና የካፒታል ገበያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ታምራት መንገሻ፤ የካፒታል ገበያ በኢኮኖሚው በቂ የገንዘብ ዝውውር የሚያስችል ነው ብለዋል።
ገበያው የኢትዮጵያን ማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን በማስተካከል ረገድም ጉልህ ሚና እንደሚኖረውና ለግልም ሆነ ለድርጅቶች በቂ የስራ ማንቀሳቀሻ ገንዘብ ለማስገኘት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በማይዋዥቅ መልኩ በዘላቂነት እንዲያድግ የፋይናንስ አገልግሎት ዘርፉን አስቻይ ሁኔታ ማስፋትና ጠንካራ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
እንደ ሳንዲ ራይትና መምህር ታምራት መንገሻ ገለጻ፤የካፒታል ገበያው ተአማኒነትን፣ግልፅነትን፣ብቃትና ቅልጥፍናን የሚፈልግ ለዚህም ጠንካራ የቁጥጥር ማዕቀፍ፣ገበያውን የሚያሳልጥ ብቁ የሰው ኃይል፣ቴክኖሎጂና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ማሟላት ያስፈልጋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና 'ቻርተርድ ኢንስቲትዩት ፎር ሴኪዩሪቲስ ኤንድ ኢንቨስትመንት' ከኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ጋር በመሆን ገበያውን መጀመር የሚያስችል የባለሙያዎች ስልጠና እየሰጡ መሆኑን አመልክተዋል።
በስልጠናው የካፒታል ገበያን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ ቀጣይነት ያለውና ውጤታማ ገበያ እንዲኖር ለማድረግ አስፈላጊው ድጋፍ መደረጉን አንስተዋል።
በዚህም የካፒታል ገበያው ተወዳዳሪና በኢንቨስተሮች እምነት የሚጣልበት ምቹ የግብይት ቦታ እንዲሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ስልጠና እና የምስክር ወረቀት እየሰጡ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የካፒታል ገበያ የውስን ባለሃብቶች ብቻ ሳይሆን የሁሉም የግብይት ቦታ እንደሚሆን በቂ ግንዛቤ እንዲኖር መሰራት እንዳለበትም አመልክተዋል።
'ቻርተርድ ኢንስቲትዩት ፎር ሴኪዩሪቲስ ኤንድ ኢንቨስትመንት' የፋይናንስና ኢንቨስትመንት ተቋም እ.አ.አ በ1992 የተመሰረተ ሲሆን በበርካታ አገራት ቅርንጫፎች አሉት።