የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከማላዊ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን በሞዛምቢክ ያደርጋል--የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከማላዊ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን በሞዛምቢክ ያደርጋል--የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
አዲስ አበባ ሚያዚያ 30/2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በኮትዲቯር አዘጋጅነት በሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከማላዊ ጋር የሚያደርገውን የሜዳ ጨዋታ በሞዛምቢክ እንደሚያካሂድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው በምድብ አራት ከግብጽ፣ ጊኒና ማላዊ ጋር ተመድባ ጨዋታዋን በማድረግ ላይ ትገኛለች።
የምድቡ አምስተኛ ጨዋታዋን ከማላዊ ጋር ሰኔ 13/2015 በሞዛምቢክ ታደርጋለች።
ጨዋታውን ለማከናወን ሞዛምቢክን ምርጫው ማድረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) ማሳወቁን ገልጿል።
ፌዴሬሽኑ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በሚገኙ ስታዲየሞች ላይ ለማከናወን ጥረት ቢያደርግም ሩዋንዳ ከዚህ በፊት ተፈቅዶላት የነበረ ስታዲየም ጊዜያዊ ፈቃድ በመነሳቱ፣ ታንዛኒያ የተሰጣት ፍቃድ የብሔራዊ ቡድኗን ጨዋታ ብቻ የምታከናውን በመሆኑ፣ ሱዳን በወቅታዊ አለመረጋጋት እንዲሁም ዩጋንዳና ኬንያ የተፈቀደ ስታዲየም አለመኖሩን አመልክቷል።
ጨዋታውን በምስራቅ አፍሪካ አገራት ማከናወን የማይቻል በመሆኑ ኢትዮጵያ ከማላዊ የምታደርገውን ጨዋታ ለማከናወን ፌዴሬሽኑ ሞዛምቢክን ምርጫ ማድረጉን ፌዴሬሽኑ ጠቁሟል።
ኢትዮጵያ ከማላዊ ጋር ባደረገችው የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ 2 ለ 1 መሸነፏ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አራት በሶስት ነጥብ የመጨረሻው አራተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።