በሲዳማ ክልል ከነገ ግንቦት 1 ጀምሮ የነዳጅ ግብይት በዲጂታል መንገድ ብቻ ይፈጸማል - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ከነገ ግንቦት 1 ጀምሮ የነዳጅ ግብይት በዲጂታል መንገድ ብቻ ይፈጸማል
ሀዋሳ፣ ሚያዚያ 30 / 2015 (ኢዜአ):-በሲዳማ ክልል ከነገ ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የነዳጅ ግብይት በዲጂታል የግብይት ብቻ እንዲፈጸም ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የሲዳማ ክልልና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮምና ንግድ ባንክ የሥራ ሃላፊዎች በሀዋሳ ከተማ በሙከራ ደረጃ የተጀመረውን የነዳጅ የዲጂታል ግብይት አገልግሎት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የንግድ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ባጢሶ ሄዲሶ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ በሚገኙ ማደያዎች በሙሉ ከነገ ጀምሮ የነዳጅ ግብይት በዲጂታል መንገድ ብቻ ይካሄዳል።
ይህንንም ለመተግበር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት በየደረጃው መደረጉን ጠቁመዋል።
የሚተገበረው የነዳጅ ግብይት ግዜን መቆጠብና ተገቢ ያልሆነ አሰራርን ማስቀረት ጨምሮ የተለያዩ ችግሮችን ለማስቀረት የላቀ ሚና እንደሚኖረው አመልክተዋል።
ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ከኢትዮ ቴሌኮምና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተመቻቸ መተግበሪያ ከአገልግሎት ፈላጊው ጋር የማስተሳሰሩ ስራ መቀጠሉን ገልጸው፤ ተጠቃሚዎችና ማደያዎች በተመቻቸው አሰራር መሰረት ግብይት በመፈጸም የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ለነዳጅ ግብይት አሰራሩ ዉጤታማነት በየደረጃዉ ያሉ ባለድርሻዎች እያደረጉት ያለዉን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
የሐዋሣ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሪት በላይነሽ ገዳም በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ማደያዎች የዲጂታል ግብይት ለማካሄድ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ በሙከራ ደረጃ ዛሬ መጀመሩን ገልጸዋል።
ከነገ ግቦት 1 ቀን ጀምሮ በከተማዋ በሚገኙ በሁሉም ማደያዎች ሁሉንም ዓይነት የነዳጅ ምርቶችን በዲጂታል ግብይት ብቻ የሚፈጸም መሆኑን አስገንዝበዋል።
ይህን ለማሳካት ከማደያ ባለቤቶች፣ ስራ አስኪያጆች፣ሠራተኞችና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር ቅንጅት በመፍጠር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸው፤ ተፈጻሚ ለማድረግ መልካም መነሳሳት እንዳለ በሙከራው ወቅት መታየቱን ጠቁመዋል።
የኢትዮ ቴሌኮም ደቡባዊ ሪጅን ስራ አስኪያጅ አቶ ጁኔድን አብድርቃድር በበኩላቸው ለአተገባበር ቀላል የሆነ መተግበሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
በየማደያው አገልግሎት ፈላጊዎች እንዳይቸገሩ የሚያግዙ ባለሙያዎች መመደባቸውን ገልጸው፤ አገልግሎቱ ቀልጣፋ በመሆኑ ለተገልጋይ እፎይታ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የዲጂታል ግብይቱ ቀላል ቀልጣፋና ለአተገባበር ምቹ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሐዋሣ ዲስትሪክት የዲጂታል ባንኪንግ ኃላፊ አቶ በቀለ ረጋሣ ናቸው።
ተጠቃሚዉ ማህበረሰብ ባለሙያዎች በሚያሳዩአቸዉ መንገዶች በመጠቀም የዲጂታል ግብይቱ ዉጤታማ እንዲሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።