ቀጥታ፡

76ኛው የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ጉባኤ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ተካሄደ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2015(ኢዜአ)፦ 76ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ጉባኤ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ተካሄደ።

የኮሚቴው ጉባኤ ላይ የተመድ ኮንቬንሽን ፀረ ስቃይ እና ሌሎች ጭካኔ የተሞላበት፣ ኢሰብአዊ፣  አያያዝ ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።

በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ የፌዴራል ፖሊስ በደህንነት ዘርፍ ሪፎርም በተለይ በሰብዓዊ መብት አያያዝና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በተጠርጣሪዎች ላይ ለሚደርስ ሰቆቃ እና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ትዕግስት እንደሌለው ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም ገልጸዋል። 

የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት በሰጠው ስልጣን መሰረት የጸጥታ ስጋቶችን ለማስወገድ እና በህብረተሰቡ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በማጣራት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም ከሪፎርሙ በፊት በምርመራው በኩል ሲፈፀሙ የነበሩ ኢሰብአዊ ድርጊቶችን አስታውሰው ለዚህም መንግስት በወሰደው እርምጃ ሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጸምበት የነበረውን ማዕከል እንዲዘጋ መደረጉን አስታውሰዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት የዜጎች ሰብዓዊ መብትን ያከበረ የምርመራ ስራ በተሻለ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሆነም ለመድረኩ አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የፖሊስ ትብብርን፣ የጋራ ስትራቴጂዎችን፣ የመረጃ ልውውጥን፣ የጋራ ስራዎችን እና የጋራ ምርመራን ለማጠናከር ከክልላዊ እና አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።

በጉባኤው ላይ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት፣ ከፍትህ ሚኒስቴር ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ የስደተኞችና ስደት ተመላሾች አገልግሎት እንዲሁም ጄኔቫ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ የተውጣጣ ልዑክ መሳተፉን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም