ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመከላከል ጥረትን ለአዳዲስ ሁነቶች የዝግጁነትና ምላሽ አቅም ከማዳበር ስራ ጋር የማጣመር ስትራቴጂን ትከተላለች - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመከላከል ጥረትን ለአዳዲስ ሁነቶች የዝግጁነትና ምላሽ አቅም ከማዳበር ስራ ጋር የማጣመር ስትራቴጂን ትከተላለች - ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሚያዝያ 30/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቀጣይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመከላከል ጥረትን ለአዳዲስ ሁነቶች የዝግጁነትና ምላሽ አቅም ከማዳበር ስራ ጋር የማጣመር ስትራቴጂን እንደምትከተል የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር በኮቪድ 19 ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥቷል።
የዓለም የጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ድንገተኛ የህብረተሰብ የጤና ስጋት አይደለም ብሎ መፈረጁ ይታወሳል።
በመሆኑም የኮቪድ 19 በሽታ እንደማንኛውም ተላላፊ የሆኑ በሽታዎች ሆኖ የሚቀጥል የጤና ጉዳይ እንደሆነም ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት ስርጭቱን ለመግታት በሽታውንና ሞትን ለመቀነስ እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የህብረተሰቡን ማህበራዊ ኢኮኖሚ እና ጤና ላይ የሚያደርሰውን አጠቃላይ ተጽእኖ ለመቀነስ ከተለያዩ አጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር ሲሰራ መቆየቱን በመግለጫው አስታውቋል።
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የኮቪድ 19 ወረርሽኝን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በሽታው ዓለም አቀፍ የህብረተሰብ ድንገተኛ የጤና ስጋት መሆኑ ቢነሳም አሁንም ለበርካቶች ሞትና ጤና ስጋት ሆኖ ይቀጥላል ሲል አሳስቧል።
ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ በቀጣይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመከላከል ጥረትን ለአዳዲስ ሁነቶች የዝግጁነትና ምላሽ አቅም ከማዳበር ስራ ጋር የማጣመር ስትራቴጂን እንደምትከተልም አስታውቋል።
በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከልና በመቆጣጠር በኩል የተገኘውን አገራዊ አቅም ማስቀጠልና ወደፊት ሊከሰቱ ለሚችሉ የጤና ችግሮች የማዳበር ስራ ይሰራል ብሏል።
የኮቪድ-19 ክትባትን ከመደበኛ የክትባት መርሃ-ግብሮች ጋር ማቀናጀት እንዲሁም የኮቪድ-19 ምላሽ ትግበራንም ከመደበኛ የጤና ፕሮግራሞች ጋር አቀናጅቶ እንደሚሰራ ገልጿል።
የህክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር፣ ተከታታይነት ያለው የማህበረሰብ ተሳትፎንና ግንዛቤን የማሳደግ ስራ እንደሚሰራም አስታውቋል።
በተጨማሪም ከአፍሪካ ሲዲሲና ከዓለም አቀፍ አካላት ጋር በመተባበር አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የህብረተሰብ ጤና ደህንነት አጀንዳዎች እንዲሁም በወረርሽኝ መከላከል፣ ዝግጁነትና ምላሽ አሰጣጥ ላይ መስራት የቀጣይ አቅጣጫዎች መሆናቸውን አመላክቷል።