ቀጥታ፡

በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መንግስት ለግሉ ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል- ሚኒስትሮች

አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2015(ኢዜአ) የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት መንግስት ለግሉ ዘርፍ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በተከፈተው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ፤ የአንደኛ ዓመት ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤቶች ዙሪያ የፓናል ውይይት ተካሂዷል። 
 
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሚያዝያ 2014 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በንቅናቄው የተገኙ ውጤቶችና የነበሩ ፈታኝ ሁኔታዎችን በማስመልከት ባለድርሻ አካላትና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል።
 



የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የማምረቻው ዘርፍን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ተወዳዳሪና ቀጣይነት እንዲኖረው ግብ ይዞ መጀመሩን አንስተዋል።
 
በዚህም የግንዛቤና የቅንጅት ስራዎች፣ የአሰራር ማሻሻያዎችና ተጨባጭ ድጋፎች በማድረግ ነባራዊ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ፈተናዎችን ተቋቁሞ እንዲራመድ ማስቻሉን ገልጸዋል።
 
"የማምረቻው ዘርፍ የችግር መውጫ በር ነው" ያሉት ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የገቢ ተኪ ምርቶች እንዲጨምሩ፣ የኤክስፖርት መጠን እንዲሻሻል፣ የማምረት አቅም እንዲጨምርና የኢንዱስትሪ ሽግግር እንዲፈጠር ማስቻሉን ገልጸዋል።
 
በማምረቻው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ዋነኛ የእድገት መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፤ የንቅናቄው ሂደት ቀጣይነት ይኖረዋል ብለዋል።
 
የፋይናንስና ጉምሩክ፣ የመሰረተ ልማትና ግብዓት፣ የአቅም ግንባታና ምርምር፣ የኢንቨስመንት፣ የፌዴራልና የክልል ቅንጅት የሚሉ አምስት ክላስተሮች ተለይተው ተቋማዊ መልክ ይዞ እንዲቀጥል ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት መቋቋሙን ጠቁመዋል።



 
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪው ፈተናዎችን በመቋቋም ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
መንግስት በዓለም አቀፍ ችግርች ጫናዎች እያሉበትም የግሉን ዘርፍ ለመደገፍ ጥረት ማድረጉን አስታውሰው፤ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፍቀድን ጨምሮ ስትራቴጂካዊ የፖሊሲ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን አንስተዋል።
 
በንግድ ባንኮች የግሉ ዘርፍ የፋይናንስ አቅርቦት በኩል ትልቅ መሻሻል መምጣቱን አውስተው፤ ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት አኳያ መሻሻሎች ቢኖሩም በቀጣይነት ብዙ መስራት ይጠይቃል ነው ያሉት።
 
ሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ጠቁመው፤ የግሉን ዘርፍ አጋዥ በሆነ አግባብ ተግባራዊ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።
 
በየትኛውም የልማት መስክ በቅንጅት መስራት ከተቻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጥሩ ማሳያ ስለመሆኑም ገልጸዋል። 



የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን የ10 ዓመት ዕቅዱን ለማሳካት የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በመፍታት ሚና እንደነበረው ጠቅሰዋል።
 
መንግስት አመቻች እንጂ አምራቹ የግሉ ዘርፍ በመሆኑ ተግዳሮቶችን በተናበበ አግባብ በመፍታት ቀጣይነት ያለው ኢንዱስትሪ ልማት ለማረጋገጥ ምቹ የፖሊሲና አሰራር ማዕቀፍ ይዘረጋልም ነው ያሉት።
 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ ዲፕሎማሲው ከልማዳዊ አካሄድ ወደ ንግድና ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዕይታውን አዙሮ ይሰራል ብለዋል።
 
የንግድና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ የኢትዮጵያ ምርቶችን ለማስተዋወቅ፣ ገበያ ለማስፋት ሁነኛ ሚና እንዳለው ገልፀው፤ ኢትዮጵያን የወከሉ ዲፕሎማቶች በዚህ ቅኝት መራመድ አለባቸው ብለዋል።
 
የፓናሉ ተሳታፊዎችም ንቅናቄው ዘርፉ ትኩረት እንዲያገኝ አወንታዊ ሚና እንደነበረው ገልጸዋል።
 
በቀጣይም መሰል ንቅናቄዎች እንዲቀጥሉና በተለይም ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦት፣ ከጉምሩክ አሰራር ችግር፣ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በውጭ ገበያ ከማስተዋወቅ አኳያ ያሉ ክፍተቶች እንዲታረሙ ጠይቀዋል።
 
የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግና የዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት የማምረቻ ዘርፉን በዘላቂነት ለመደገፍ መንግስት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም