የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በወንጀል መከላከል ዘርፍ ያሰለጠናቸውን የፖሊስ አባላት አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በወንጀል መከላከል ዘርፍ ያሰለጠናቸውን የፖሊስ አባላት አስመረቀ
አዲስ አበባ ሚያዚያ 29/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በወንጀል መከላከል ዘርፍ ያሰለጠናቸውን የፖሊስ አባላት አስመረቀ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በአዋሽ ሰባት መሰረታዊ የፖሊስ ስልጠና አካዳሚ ለረጅም ጊዜ ያሰለጠናቸውን የወንጀል መከላከል የአድማ ብተና ፖሊስ አባላትን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የፀጥታና ጥበቃ ዋና መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር አበራ ሁንዴ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይም ባደረጉት ንግግርም የዛሬ ተመራቂ የፖሊስ አመራርና አባላት ስልጠናውን በሚገባ ተከታትለው በብቃት ያጠናቀቁ የተሰጣቸውንም ፈተና በሚገባ ያለፋ መሆናቸውን ገልፀዋል።
“የሀገራችንን ሰላም እና ፀጥታ በማረጋገጥ በኩል የፀጥታና ህግ ማስከበር መምሪያ የህግ ማስከበር ስራዎችን በጀግንነት፣ በግልፀኝነትና በቅንነት ስታገለግሉ ቆይታችሁ ግዳጃችሁን ፍጹም በጥሩ ሥነ-ምግባር ፈፅማችሁ ወደ መጀመሪያው የአድማ ብተና የፖሊስ ሙያ በመመለስ ለቀጣይ ሀገራዊ ተልዕኮ የተዘጋጃችሁ በመሆናችሁ ኩራት ይገባችኋል” ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ አክለውም ከዚህ በፊት የነበሩት ግዳጆች ፈተና እንደነበራቸውና ህግ ለማስከበር ህዝብና መንግስት የጣለብንን አደራ ለመወጣት የተከፈሉ መስዋእትነቶች እንደማይረሱ ተናግረዋል።
አያይዘውም በቀጣይ የሚጠብቁን ግዳጆችን በብቃት ለመወጣት ቁርጠኝነት የሚጠይቅ በመሆኑ ሙያዊ ሥነ-ምግባር በተላበሰ ፖሊሳዊ ጨዋነት ከማንኛውም የሀይማኖት፣ የዘርና የፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ የፖሊስ አገልግሎት ለመስጠት ከአድማ መከላከልና መቆጣጠር ፖሊስ ይጠበቃል ብለዋል።
አሁን ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ ከአንድ ፈተና ወደ ሌላ ፈተና እየተሸጋገረች ያለች በመሆኗ ፈተናውን ለመወጣት በፖሊስ ሙያና ስነ-ምግባር መስራት ይጠበቅብናል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፖሊስ ሁኔታዎችን በማገናዘብ ሀገሩን በፍጹም ኢትዮጵያዊነት ለማሻገር መስራት አለበት ሲሉም አክለዋል።
የግጭት አወጋገድ ሥርዓታችን በበሳል የአመራር እና የተመሪ ጥበብ የታከለበት ሊሆን ይገባል ሲሉም ምክትል ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የአዋሽ 7 አመራር አቅም ግንባታ ማሰልጠኛ ማዕከል ዋና ክፍል ኮማንደር ከበደ ለገሰ በዕለቱ የስልጠና ሪፖርት አቅርበዋል።
በዚህም ተመራቂዎቹ በቆይታቸው በአድማ ጊዜ ትዕዛዝ አጠባበቅ፣ ተመጣጣኝ እርምጃ አወሳሰድ፣ የእምነት፣ ትምህርት ቤቶችንና ሆስፒታሎች አካባቢ እንዴት አድማ መከላከልና መቆጣጠር እንደሚገባ ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አሰላለፍና የተተኳሽ መሳሣሪያ አጠቃቀም፣ ፖሊሳዊ ስነ-ምግባር፣ በህገ-መንግስት፣ የወንጀል መከላከል ትምህርቶች፣ የአካል ብቃት ስልጠና መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።
በመጨረሻም ስልጠናው እንዲሳካ እገዛ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት የዕውቅና እና የምስጋና ምስክር ወረቀት እንዲሁም ስጦታ መበርከቱን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።