ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በብዛትና በጥራት ለማምረት ግብርናው በቴክኖሎጂ መዘመን አለበት--ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ - ኢዜአ አማርኛ
ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በብዛትና በጥራት ለማምረት ግብርናው በቴክኖሎጂ መዘመን አለበት--ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ
በሳይንስና ቴክኖሎጂ የዘመነ ግብርና የመገንባት ሂደት የዘርፉ ዋነኛ ትኩረት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29/2015(ኢዜአ)፦ ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በብዛትና በጥራት ለማምረት ግብርናው በቴክኖሎጂ መዘመን እንደሚገባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
የግብርናው ዘርፍ እስካሁን የመጣበትን፣ አሁን የደረሰበትን የእድገት ደረጃና የቀጣይ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን የሚያሳይ የግብርናና ሳይንስ ኢግዚቢሽን ዛሬ በሳይንስ ሙዚየም ተከፍቷል፡፡
በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እነዚህንና ሌሎች ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በብዛትና በጥራት ለማምረት ግብርናው በቴክኖሎጂ የዘመነ መሆን ይገባዋል ማለታቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
የግብርና ሳይንስ ኢግዚቢሽኑን በይፋ የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ግብርና ህይወት ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ይጠቁማል።
የሰው ልጅ በየትኛውም ደረጃና ጊዜ የማይተዋቸው ምግብ፣ ልብስና መድኃኒት ምንጫቸው የግብርና ምርት መሆኑን መናገራቸውንም አክሏል፡፡
እስካሁን የተሄደበትንና አሁን ያለንበትን የግብርና ቴክኖሎጂ አቅም የሚያሳይ ኤግዚቢሽን በመዘጋጀቱ መደሰታቸውን መግለጻቸውንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ኢግዚቢሽኑ ግብርና ከተለያዩ ሳይንሶች ጋር ያለውን ግንኙነት ያሳየና የግብርና ሳይንሳዊ አጠቃቀምና አተገባበር ላይ ትምህርት የሚገኝበት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ በስንዴና ሌሎች ሰብሎች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ በቡናና በእንስሳት ምርት ከአፍሪካ ግንባር ቀደም መሆኗን መግለጻቸውንም እንዲሁ።
እነዚህን ምርቶች በተሻለ ቴክኖሎጂ በማምረትና የገበያ ትስስር በመፍጠር የተሻለ ምርትና ምርታማነት እንዲሁም ገቢ ለማግኘት የግብርና ሳይንስ ያለበትን ደረጃ እና አጠቃቀም በግልፅ ማወቅ ይገባል ማለታቸውንም ጠቁሟል፡፡
ለዚህም ይህ የግብርና ሳይንስ ኢግዚቢሽን አንዱና ትልቁ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የግብርና ምርትና ምርታማነትን በሁሉም ዘርፍ በመጨመር የምግብ ዋስትናን ከመሸፈን ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚቻል መግለጻቸውንም መረጃው ጠቁሟል፡፡
ይህን ለማሳካት በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ ማነቆ የሆኑትን የአፈር ለምነትና ሌሎች ችግሮችን ሳንሳዊ መንገድ በመከተል መፍታት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን አስታውቋል፡፡
የግብርና ሳይንስ ኢግዚቢሽኑን ተማሪዎች፣ ወጣቶች፣ ተመራማሪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው ሁሉ ግብርና እንዴት ተጀመረ፣ አሁን ያለበትን ደረጃና የቀጣይ ጉዞውን በተመለከተ በሳይንስ ሙዚየም በመገኘት አስደናቂ የግብርና ሳይንሶችን እንዲመለከቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ማቅረባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡