ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪው ፈተናዎችን በመቋቋም ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት ሆኗል - የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2015(ኢዜአ)፦ ለአንድ አመት የተከናወነው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪው ፈተናዎችን በመቋቋም ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት ሆኗል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ።

በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በተከፈተው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ፤ አንድ ዓመት ባስቆጠረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤቶች ዙሪያ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኙ ውጤቶችና የነበሩ ፈተናዎችን በማስመልከት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ነው ውይይቱ እየተካሄደ ያለው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ፤ የተናበበና የተቀናጀ ስራ ከመስራት አኳያ በአንድ ዓመት ውስጥ የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል።

የማኑፋክቸሪንግ ልማት ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ስኬት የበኩሉን ሚና የሚወጣ በመሆኑ የግሉ ዘርፍ እንዲጎለብትና የዕድገት አማራጮችን ለማስፋት የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

እንደ አጠቃላይ ለአንድ አመት የተከናወነው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪው ፈተናዎችን በመቋቋም ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚ ዕድገት መሰረት ሆኗል ነው ያሉት።

ሁለተኛው ምዕራፍ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ጠቁመው ለዚህም አጋዥ በሆነ አግባብ ዘርፉን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ለግሉ ዘርፍ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሩ ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት አኳያ በቀጣይነት ብዙ መስራት ይጠይቃል ነው ያሉት።

የቀጣናው ህዝብ ብዛት፣ ምቹ መልክዓ ምድራዊ አቀማምጥ፣ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠናን ጨምሮ የገበያ ዕድሎች ለዘርፉ ዕድገት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ጠቁመው፤ መንግስት የማምረቻውን ዘርፍ ማሳደግ የሚያስችሉ ስተራቴጂካዊ ስራዎች እያከናወነ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።

የውጭ ምንዛሪን ጨምሮ የፋይናንስ አቅርቦት ማሳደግ፣ የገቢ ምርት ተኪ ምርቶችን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በየትኛውም የልማት መስክ በቅንጅት መስራት ከተቻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጥሩ ማሳያ ስለመሆኑም ገልጸዋል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል በበኩላቸው የማምረቻው ዘርፍ ተወዳዳሪና ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንዲያመጣ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘርፉ ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎችን ተቋቁሞ እንዲራመድ ማስቻል፣ ጠንካራና የተቀናጀ የማምረቻ ዘርፍ ስርዓት ማመቻቸት፣ ለ10 ዓመቱ ዕቅድ ስኬት ምቹ ሁኔታ እና በቂ ግንዛቤ መፍጠር ከንቅናቄው ዓላማዎች መካከል መሆናቸውን አብራርተዋል።

በዚህም በንቅናቄው የፌዴራልና የክልል ተቋማት ቅንጅት እንዲመጣና ውጤታማ የግንዛቤ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፤ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የዘርፉን ተግዳሮቶች በመቅረፍ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን መሰረት ያኖረ መሆኑን ጠቁመዋል።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ገበያ ለማስፋት፣ የንግድና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያን የወከሉ ዲፕሎማቶች ሁሉ በዚህ ቅኝት መራመድ አለባቸው ብለዋል።

በአፍሪካና በሌሎችም ክፍለ ዓለማት ያሉ ኤምባሲዎችና ዲፕሎማቶች የገበያ መዳረሻዎችን የማስፋትና የኢትዮጵያን ምርቶች በስፋት የማስተዋወቅ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም