ቀጥታ፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቦንድ የሚገዙበት መርሃ ግብር ተጀመረ

ድሬዳዋ ሚያዝያ 28/2015(ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቦንድ የሚገዙበት የአንድ ሣምንት  መርሃ ግብር ተጀመረ።

"ወጣቱ ለህዳሴው፤እኔም ድርሻ አለኝ" በሚል መሪ ሐሳብ በሚካሄደው መርሃ ግብር 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ መታቀዱን በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።


 

የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ የወጣቶች ሊግ ባዘጋጀው መርሃ ግብር በመክፈቻው ቀን ብቻ የ100 ሺህ ብር ሽያጭ ተከናውኗል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተሳተፉት የሊጉ አመራሮችና አባላት ለኢዜአ እንደተናገሩት ፤የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዘመኑ ትውልድ ተቀናጅቶ የራሱን ታሪካዊ ድል እያስመዘገበበት የሚገኝበት ፕሮጀክት ነው።

ወጣት ነስረዲን አሚን እንዳለው፤ አገር ገንቢውና ተረካቢ ወጣቱ ትውልድ የታላቁን የህዳሴ ግድብ በጉልበቱ ፣በገንዘቡና በዕውቀቱ ዳር ለማድረስ የድርሻውን መወጣት አለበት ያለ ሲሆን እሱም ቦንድ በመግዛት የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልጿል።

ወጣት ዘመድኩን አሰፋ፤ ግድቡ ለኢትዮጵያ ሁለተናዊ ዕድገት ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልጾ፣ ''እኔና እኔን መሰል ወጣቶች ተስፋ የጣልንበት ፕሮጀክት ነው'' ብሏል።

"የህዳሴውን ግድብ በተባባረ ኢትዮጵያዊ መንፈስ እንደጀመርነው፤ በተቀናጀ አንድነት እንጨርሰዋለን" ሲልም አክሏል።

የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ እውን በማድረግ የወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የህዳሴው ግድብ ምላሽና ውጤት ያመጣል ያለው ደግሞ ወጣት ናስር አህመድ ነው።

"እኛ ወጣቶች ኃላፊነታችንን እንወጣለን" ሲልም በቦንድ ግዢው መሳተፉን ተናግሯል።

ወጣት ቤዛ ዳኘው በበኩሏ ለኢትዮጵያ ከፍታና ልዕልና ወሳኝ የሆነውን የህዳሴው ግድብ ለማጠናቀቅ እስከመጨረሻው ድረስ የድርሻችንን እንወጣለን ብላለች።

''ግድቡ ለአገር ዕድገት ወሳኝ ሚና አለው" ስትልም አስተያየቷን ሰጥታለች።

የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ኮሚሽነር ፊራኦል ቡልቻ ሥነ ሥርዓቱን ካስጀመሩ በኋላ የድሬዳዋ ወጣቶች የህዳሴው ግድብ መሠረት ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ እያደረጉት ያለው ድጋፍ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ እየተካሄደ ባለው የቦንድ ሽያጭ መርሃ ግብር ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቦንድ ግዢና በስጦታ ከ96 ሚሊዮን ብር በላይ ማበርከታቸውን ከአስተዳደሩ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም