በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አራት ሺህ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል - አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አራት ሺህ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል - አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ ሚያዚያ 28/2015(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለአራት ሺህ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ፈቃድ መሰጠቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል አመለከቱ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ ታምርት አገር አቀፍ ንቅናቄ አንደኛ ዓመትን አስመልክቶ በሚሊኒየም አዳራሽ የተዘጋጀውን የንግድ ኤክስፖ መርቀው ከፍተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ለአምራች ዘርፉ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በመለየት ተከታታይነት ያለው መፍትሔ መስጠት የንቅናቄው ተቀዳሚ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።
ንቅናቄው የዘርፉን ማነቆዎች በመለየት አምራችነትን መገለጫ ባህል የማድረግ ተልዕኮ የያዘ ነውም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ያሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ ጸጋ በመጠቀም ፈጣን እድገት እንድታስመዘግብ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በሂደቱም በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመለየት ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ የመፍትሔ አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ስራ አቁመው የነበሩና ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረጉ ከ352 በላይ ኢንዱስትሪዎችን እንዲሁም 635 አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸውንም በመጠቆም።
4 ሺህ የሚሆኑ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመግባት ፈቃድ መሰጠቱም ከንቅናቄው ውጤታማ ተግባራት መካከል በማሳያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።
አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር እያደገ መምጣቱንና በንቅናቄው የተገኙ ውጤታማ ተግባራትም ቀጣይነት ባለው መልኩ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን 70 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም 54 መካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ምርትና አገልግሎታቸውን እንደሚያስተዋውቁበት ይጠበቃል።
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን አቅም ማስተዋወቅና የንግድ ትስስርን ማስፋት በንግድ ኤክስፖው ለማሳካት የተያዙ እቅዶች ናቸው።