ቀጥታ፡

አየር መንገዱ የስካይ ላይት ሆቴሎችን መለያ ብራንድ በሀገር ውስጥና በአፍሪካ ለማስፋት እየሰራ ነው - የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ ግርማ ዋቄ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 28/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ  የስካይ ላይት ሆቴሎችን መለያ ብራንድ በሀገር ውስጥና በአፍሪካ ለማስፋት እየሰራ  መሆኑን የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ ግርማ ዋቄ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አካል የሆነው የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ምዕራፍ ሁለት በትላንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  ዐቢይ አህመድ በተገኙበት መመረቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ ከዚህ ቀደም በአቪዬሽን መስክ እንደ አህጉር ስኬታማ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

በዚህም አየር መንገዱ፣ ኢትዮጵያን ከተቀረው ዓለም በማገናኘት፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት፣  የሀገሪቷን የወጪ ንግድ በማሳለጥ ረገድ የበኩሉን ሚና ሲወጣ ቆይቷል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅትም አየር መንገዱ የአየር ትራንስፖርትና ቱሪዝም ትስስራቸው ሰፊ መሆኑን በመረዳት፤ የደንበኞቹን ፍላጎት ከግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ በቱሪዝም መስክ የላቀ ውጤት ለማምጣት እየሰራ ነው ብለዋል። 

በዚህም አየር መንገዱ የስካይ ላይት ሆቴልን በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉን ገልጸው ሆቴሉ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ ስመ-ጥር ለመሆን መብቃቱንም ተናግረዋል። 


 

ይህ ጅማሮ ነው ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው፤ በቀጣይም የስካይ ላይት ሆቴሎችን በአገር ውስጥ የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎችና በአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት የመገንባት ትልም ተይዞ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አየር መንገዱ በአቪዬሽን መስክ በአፍሪካ ስመ-ጥር ለመሆን እንደበቃ ሁሉ፤ የስካይ ላይት ሆቴሎችንም  ስም የመትከል ራዕይ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ አዲስ አበባንም ሆነ ሌሎች የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎችን በማስተዋወቅና በመሥራት የቱሪዝም መስኩን ለማሳደግ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ነገር ግን የቱሪስት ፍሰት የሚኖረው ሰላማዊ በሆነ አካባቢ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መንግሥትና ሕዝብ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ስካይ ላይት ሆቴል በምእራፍ ሁለት ማስፋፊያው 651 የመኝታ ክፍሎች ፤ የስብሰባ አዳራሾች፣ የጤና ማዕከላት፣ ምግብ ቤቶችና የመዝኛኛ ሥፍራዎችን አካቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም