ቀጥታ፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተጻፉት መደመር ላይ ያጠነጠኑ መጻሕፍት አገር ለመገንባት የሚያስችሉ ሀሳቦች የተካተቱባቸው ናቸው - ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም

አዲስ አበባ ሚያዚያ 28/2015(ኢዜአ)፡- በጠቅላይ ሚኒስትር  ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተጻፉት መደመር ላይ ያጠነጠኑት መጻሕፍት አገር ለመገንባት የሚያስችሉ ትልልቅ ሀሳቦች የተካተቱባቸው  መሆናቸውን ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም ተናገሩ። 

"ቃል፤ ተግባር፤ ትውልድ " በሚል መሪ ሀሳብ በአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት እየተካሄደ ያለው አውደ-ርዕይ እንደቀጠለ ነው።  

በአውደ-ርዕዩ ላይ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተገኙ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ላይ ያተኮሩ መጻሕፍት ቀርበዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ጊዜያት ያደረጓቸውን ንግግሮች በመሰነድ የተዘጋጁ መጻሕፍት ለንባብ በቅተዋል፤ ውይይትም ተካሂዶባቸዋል።       

በዛሬው ዕለትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በመደመር እሳቤ ላይ የጻፏቸው ሦስት መጻሕፍት በውስጣቸው የያዟቸው ሀሳቦችና ለአገር በሚኖራቸው አበርክቶ ዙሪያ ሰፋ ያለ ገለፃ ተሰጥቷል።    

በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ለረዥም ዓመታት በመምህርነት ያገለገሉት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም በመጻሕፍቱ ዙሪያ ዳሰሳ አቅርበዋል።    

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ መደመር ላይ ያተኮሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ መጻሕፍት ለኢትዮጵያ ችግሮች ወሳኙ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ከራሷ የሚመነጭ መፍትሔ መሆኑን ያመላከቱ ናቸው ብለዋል።   

ለዚህ ደግሞ በዘር፣ በሃይማኖትና ሌሎች ጉዳዮች ሳንለያይ በጋራ አገር መገንባት እንደሚገባ በግልጽ የሚያሳዩ መሆናቸውንም አብራርተዋል።          

የመደመር ፍልስፍና ዜጎችን በማስተባበር ለአንድ ዓላማ እና ግብ የሚያሰልፉ ሀሳቦችን የያዘ ስለ መሆኑም ነው ያብራሩት።    

መደመር፣ የመደመር መንገድና የመደመር ትውልድ መጻሕፍት ኢትዮጵያ ወደ ብልጽግና ማማ ለመውጣት ልትከተላቸው የሚገቡ መንገዶችን  ያስቀመጡ ትልቅ ሥራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።    

ሩቅ ለመጓዝ አብሮ መጓዝ የሚለውን መርህ በመከተልም በአንድነት መሥራት እንደሚገባ መጻሕፍቱ እንደሚዳስሱ ጠቁመው፤ ፍቅር፣ መቻቻል እንዲሁም ከጥላቻ መራቅ ትልቅ አገር ለመገንባት ወሳኝ መንገዶች መሆናቸውንም የሚሳይ ጥልቅ ሀሳቦች የተካተቱባቸው ናቸው ብለዋል።

አሜሪካ በዓለም ላይ ትልቅ አገር መሆን የቻለችው ከተለያዩ አገራት የሄዱ ዜጎች ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ሳይሉ በመሥራታቸው መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፤ የመደመር እሳቤም ይህን የሚያጠናክር መሆኑን አክለዋል።      

አለመተማመንና መጠራጠር የመደመር ጽንሰ-ሀሳብ መሬት እንዳይወርድ ከሚያደርጉ ጉዳዮች መካከል መሆኑን ጠቁመው፤ ይህን አስተሳሰብ መቀየር እንደሚገባም ነው አጽንዖት የሰጡት።

"መደመር ኃይል መሆኑን፤ መደመር ጉልበት መሆኑን፤ ከተረዳን የመደመር እሳቤን መሬት ለማውረድ አይከብድም" ያሉት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ለዚህ ደግሞ ልቦናችንን ክፍት በማድረግ መተግበር ይጠበቃል ብለዋል።   

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቷን ለመለወጥ ቴክኖሎጂና ዕውቀት መር አካሄድ መከተል እንደሚገባ በመጽሐፎቻቸው ያስቀመጡበት መንገድ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠታቸውን እንደሚያመላክትም አክለዋል። 

 

  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም