በኢትዮጵያ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ምቹ የሆነ አውድ ተፈጥሯል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ምቹ የሆነ አውድ ተፈጥሯል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 28/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ በሚገኘው ውጤታማ ስራ ለዘርፉ ምቹ የሆነ አውድ መፈጠሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተዘጋጀውን ኢትዮጵያ ታምርት አገር አቀፍ ኤክስፖ መርቀው ከፍተዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የክልል ርዕሳነ-መስተዳደሮች፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች እና ሌሎች የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ ማምረት ትችላለች የምንለው በቂ መሬትና ማምረት የሚችል በቂ የሰው ኃይል ስላላት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።
በንጽጽር ሲታይም በአሁኑ ወቅት አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍ የሚያስችል የተሻለ የፋይናንስ እና የኃይል አቅርቦት አቅም እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
የአምራች ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ በሚገኘው ውጤታማ ስራ ኢትዮጵያ ለአምራች ኢንዱስትሪው ምቹ የሆነችበት አውድ መፈጠሩን ተናግረዋል።
በማዕድን ዘርፍ የነበሩ መቀዛቀዞችን በማነቃቃት በርካታ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ምርቶች እየተመረቱ ይገኛሉ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ለአብነትም በቀጣይ ዓመት የሚመረቀው ለሚ የሲሚንቶ ፋብሪካ አሁን ኢትዮጵያ የምታመርተውን ሲሚንቶ ከ50 በመቶ በላይ ያሳድገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ እየተፈጠረ የሚገኘውን አስቻይ ሁኔታ በመጠቀም ግጭት፣ ጥላቻና መራራቅን በመተው ልማት እና ፈጠራን ማበረታታት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ዓለም ካለችበት አስፈሪ ሁኔታ አንጻር የተዘጋጀ፣ ያመረተ እና የሰከነ አገር እንደሚሻገርም አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከፍተኛ ዕድገት እያመጡ ካሉ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ጠቁመው፤ በማዕድን፣ በኢንዱስትሪና በሰው ኃብት ልማት ላይ ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚከናወንም ነው የገለጹት።
የሚከናወኑ ውጤታማ የልማት ስራዎች ፈተና አልባ አለመሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ፈተናዎችን በሕብረት በማሸነፍ የበለጸገች እና የጸናች አገርን ለትውልድ እናሸጋግራለን ብለዋል።
በሚሊኒየም አዳራሽ በይፋ የተከፈተው አገር አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት ይቆያል።
በኤክስፖው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለው አቅም የሚተዋወቅበት፣ የንግድ ትስስር የሚፈጠርበትና የዘርፉን ማነቆዎች በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ይቀመጥበታል የተባለ የፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 124 አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርትና አገልግሎታቸውን እንደሚያቀርቡ ተመላክቷል።