ፖሊስነት ከራስ በላይ ሕይወትን ለሕዝብ የሚሰጥ የከበረ ሙያ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ፖሊስነት ከራስ በላይ ሕይወትን ለሕዝብ የሚሰጥ የከበረ ሙያ ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 28/2015(ኢዜአ)፦ ፖሊስነት ከራስ በላይ ሕይወትን ለሕዝብ የሚሰጥ የከበረ እና አገልግሎቱም የላቀ ሙያ መሆኑን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በአዲስ አበባ ፖሊስ አካዳሚ ለ27ኛ ዙር ሲያሰለጥናቸው የቆዩ የመደበኛና አድማ ብተና የፖሊስ ሠራዊት አባላትን አስመርቋል።
በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ለምርቃት ለበቁ የፖሊስ አባላት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከንቲባዋ ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ የመዲናዋን ነዋሪዎች ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ የሚያስችል የለውጥ ትግበራ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
"ፖሊስነት የከበረ ሙያ ነው፤ አገልግሎቱም የላቀ ነው" ያሉት ከንቲባዋ ምሩቃን የፖሊስ ሠራዊት አባላት በሚሰጣቸው የሥራ ስምሪት ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ መሥራት እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል።
ሙያውንም የከበረና የላቀ የሚያደርገው ከራስ በላይ ለሕዝብ በሚል መርህ በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል በመቻሉ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሕይወት መስዋዕትነት ወደ ሚጠይቀው ሙያ የተቀላቀሉ የፖሊስ አባላትም ሕዝብን በቅንነት፣ በታማኝነትና በእኩልነት መርህ ማገልገል እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ፤ ዘመናዊ የፖሊስ አደረጃጀት በማዋቀር ወንጀልና ወንጀል ነክ ጉዳዮችን መከላከልና ምላሽ መስጠት የሚቻልበት የአሠራር ሥርዓት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
መዲናዋ የተለያዩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በብቃት እያስተናገደች እንደምትገኝ ጠቁመው፤ ለሁነቶቹ ሰላማዊነትም የፖሊስ ሠራዊቱ ግዳጁን በከፍተኛ ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ አካዳሚ የ27ኛ ዙር ምሩቅ የፖሊስ አባላት ከቀደምት የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ለሕዝባቸው ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፤ ሰላም በየትኛውም አገርና ከተማ ለሚኖሩ ሰዎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑም የመዲናዋን ነዋሪዎች ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት አክብሮ የሚያስከብር ፍሬያማ የፖሊስ ሠራዊት ግንባታ ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሕግ የበላይነት መርህ ዜጎች ያለ አንዳች መድልዎ በሰላም እንዲኖሩ ማስቻል የፖሊስ ተቀዳሚ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ተመራቂ የፖሊስ አባላትም የመዲናዋ ነዋሪዎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ በማድረግ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በሚገባ መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር መኮንን አሻግሬ፤ የንድፈ-ሃሳብ እና የተግባር ትምህርታቸውን የተከታተሉ ብቁ የፖሊስ አባላት ለምርቃት መብቃታቸውን አስታውቀዋል።
በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እና ሌሎች የፖሊስ መኮንኖችና የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።