ፍላጎትን በሀይል ለማስፈጸም መሞከር የፍትህ ስርአቱን ስለሚጎዳ ሕገ ወጥ ቡድኖች ላይ የሚወሰደው እርምጃ መጠናከር አለበት--የህግ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
ፍላጎትን በሀይል ለማስፈጸም መሞከር የፍትህ ስርአቱን ስለሚጎዳ ሕገ ወጥ ቡድኖች ላይ የሚወሰደው እርምጃ መጠናከር አለበት--የህግ ባለሙያዎች
ጅማ ሚያዝያ 28/2015(ኢዜአ) በህገ ወጥ መንገድ ተደራጅተው ፍላጎታቸውን በሀይል ለማስፈጸም የሚሞክሩ አካላት የፍትህ ስርአቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ስለሚያሳድሩ ሕገ ወጥ ቡድኖች ላይ የሚወሰደው እርምጃ መጠናከር አለበት ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ተናገሩ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ህገ ወጥ የጥፋት ቡድኖች በሚፈጽሙት ወንጀልና ሁኔታው የሚያስከትለው ስርአት አልበኝነት የዜጎችን ፍትህ የማግኘት መብት የሚጋፋ ነው ብለዋል።
የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህር አገኘው ወልደስላሴ እንዳሉት ፍላጎትን በጉልበት ለማስፈጸም የሚጥሩ ጽንፍ የያዙ አካላት ትክክለኛ ፍትህ ተደራሽ እንዳይሆን ያደርጋሉ።
በሀይል ፍላጎትን ለማስፈጸም መነሳት ለአገርና ለህዝብ ጠቃሚ አለመሆኑንም የገለጹት መምህሩ መንግስት የህገ ወጥ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለማስቆም የጀመረውን ስራ ማጠናከር አለበት ብለዋል።
የእነዚህ ቡድኖች ድርጊት ዜጎች በሀገራቸው ህግ ላይ እምነት እንዳይኖራቸው ስለሚያደርግ እነዚህን የጥፋት ቡደኖች ማስቆም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ መንግስት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የጀመራቸው ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህንን መንገድ ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሌላው በጅማ ከተማ ፍርድ ቤት የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አስፋው ተስፋዬ በበኩላቸው "በደቦ ፍርድ የሰዎችን ውድ ህይወት መቅጠፍ፣ ንብረት ማውደምና ዜጎችን ማፈናቀል ተቀባይነት የሌላቸው የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ድርጊቶች ናቸው" ብለዋል።
በተለይ ተደራጅተው ህገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙና ፍላጎታቸውን በሀይል ለማሳካት የሚሰሩ አካላት ዜጎች የፍትህ ሥርዓቱን እንዲጠራጠሩና ፍትሕ የሌለ ያስመስላሉ ነው ያሉት።
በሀገራችን የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት ጥሩ መሆኑን የገለጹት አቶ አስፋው፣ የሀይል ድርጊቶች ነገሮችን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ከመውሰድ ያለፈ ሚና አይኖራቸውም ብለዋል።
በመሆኑም ችግሮችን በህግ ጥላ ስር ብቻ መፍታት ለአገርና ለህዝብ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ አስፋው አብራርተዋል።
''በሀገራችን የተለያየ ጽንፍ ይዘው እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል የጥፋት ተግባር እየፈጸሙ ያሉ ሀይሎች ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው ብለዋል።
መንግስትም በተለያየ መልኩ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ ማጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።