ኢትዮጵያ በአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በአርዓያነትና በትብብር መስራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች-ዶክተር ግርማ አመንቴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በአርዓያነትና በትብብር መስራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች-ዶክተር ግርማ አመንቴ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 28/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በአርዓያነትና በትብብር መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ ገለጹ።
በዓለም ላይ ካለው የሚታረስ መሬት 65 በመቶ የሚሆነው አፍሪካ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም አህጉሪቷ አሁንም የምግብ ሉዓላዊነቷን አላረጋገጠችም።
ኢትዮጵያ በአስር ዓመት የልማት ዕቅዷ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ጀምሮ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን ግብ አስቀምጣ እየሰራች ትገኛለች።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ አፍሪካውያንን ለፀረ ቅኝ ግዛት ትግል በማነሳሳት ነጻነታቸውን እንዲቀዳጁ የነበራትን ከፍተኛ ሚና አሁንም አህጉራዊ የኢኮኖሚ ነጻነትን ለማረጋገጥ በግንባር ቀደምትነት እየሰራች ነው ብለዋል።
በተለይም በኢትዮጵያ ጦም የሚያደር መሬት እንዳይኖር በቁርጠኝነት በመስራትና ያሉ የግብርና አቅሞችን አሟጦ በመጠቀም የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የጀመረችው ስኬታማ ጉዞ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተምሳሌት እንደሚሆን ገልጸዋል።
በአስር ዓመት ዕቅዱ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች ግብርና አንዱ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል በግብአት አቅርቦትና ዘርፉን በማዘመን የተከናወኑ ተግባራት ስኬት እያስመዘገቡ እንደሚገኝ ነው ዶክተር ግርማ የገለጹት።
ኢትዮጵያ ስንዴን ከውጭ ለማስገባት በዓመት እስከ 1 ቢሊየን ዶላር ታወጣ እንደነበር አስታውሰው፤ ዛሬ ላይ ይህንን ገንዘብ ከማስቀረት አልፋ ወደ ውጭ መላክ መጀመሯን ጠቅሰዋል።
ለዓመታት በዝናብ ላይ የተመሰረተውን የኢትዮጵያ ግብርና ለመቀየር በበጋ መስኖ የተጀመሩ ስራዎች አበረታች ለውጥ እያመጡ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በግብርናው ዘርፍ ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት የተመዘገቡ ለውጦች ከአገር አልፈው ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ተሞክሮ እየሆኑ መምጣታቸውንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያገኘቻቸውን ልምድና ተሞክሮዎች በፓን-አፍሪካኒዝም መንፈስ በማጋራት እንደ አህጉር በምግብ ራስን ለመቻል በትብብር መሥራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።
አፍሪካ ያላትን እምቅ አቅምና የተፈጥሮ ፀጋ አልምታ ወደ ብልጽግና የምትሄድበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።
ለዚህም ትብብርና አጋርነትን በማጠናከር እንደ አህጉር አብሮ በማደግ የአፍሪካን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።