የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን በቀጣይ ሳምንት ወደ ፓኪስታን ሊያመራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን በቀጣይ ሳምንት ወደ ፓኪስታን ሊያመራ ነው
አዲስ አበባ ሚያዚያ 28/2015(ኢዜአ):-ከ60 በላይ አባላት ያሉት የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን በቀጣይ ሳምንት ወደ ፓኪስታን እንደሚያቀና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ጉብኝቱ በኢትዮጵያ እና ፓኪስታን መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነትና ትብብር የማጠናከር አላማ እንዳለው ገልጿል።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ጉብኝቱን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
ልዑካን ቡድኑ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ፣የተለያዩ ተቋማት ተወካዮችና የንግዱ ማህበረሰብን ጨምሮ ከ60 በላይ አባላትን እንደያዘ አምባሳደር ጀማል ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና ፓኪስታን መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ ያስችላል የተባሉ ሁለት የቢዝነስ ፎረሞች በኢስላማባድና ካራቺ ከተሞች እንደሚካሄዱም አመልክተዋል።
በፎረሞቹ ላይ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን አባላት እንደሚሳተፉና በዚህም ከፓኪስታን አቻዎቻቸው ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን ውይይቶች በማድረግ ግንኙነቶችን የሚፈጥሩበት አማራጭ እንደሚያገኙም ተገልጿል።
ኢትዮጵያና ፓኪስታን በሳይንስ፣ቴክኖሎጂና ቱሪዝምን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ያስችላሉ የተባሉ የመግባቢያ ሰነዶችን እንደሚፈራረሙም ነው አምባሳደር ጀማል ያመለከቱት።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እያደገ መምጣቱንና ይበልጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ትብብሩን ለማሳደግ በሁለቱም በኩል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው ተጠቁሟል።
የዚህም አካል የሆነውና በርካታ የፓኪስታን የንግድ ማህበረሰብ አባላትን ያካተተ ቡድን በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝትና በአዲስ አበባም የቢዝነስ ጉባኤ ማካሄዱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።