በወላይታ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 17 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ንቅናቄ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 17 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ንቅናቄ እየተካሄደ ነው
ሶዶ፣ ሚያዚያ 28 / 2015 (ኢዜአ) በወላይታ ዞን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 17 ሚሊዮን ብር የማሰባሰብ ዓላማ ያለው ንቅናቄ እየተካሄደ እንደሆነ የዞኑ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዘርገነ ወይሻ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የንቅናቄውን ዓላማ ለማሳካት የሚያስችል ነው።
በዞኑ ከሚያዚያ 20 እስከ ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በሚካሄደው የህዳሴ ግድብ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ የቦንድ ግዢ እየተካሄደ እንደሆነ ተናግረዋል።
በየደረጃው የሚገኙ ሥራ አመራሮች የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ እንደ ሀገር የሚኖረውን ላቅ ያለ ፋይዳ ህዝቡ እንዲገነዘብ ለማድረግ እየሠሩ እንደሆነ ገልጸው፤ በዚህም የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
የዞኑ ነዋሪዎች ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዥና በስጦታ መልክ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ አሁንም በንቃት ተሳትፎ እያደረጉ በመሆኑ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 17 ሚሊዮን ብር የማሰባሰብ ሥራው እንደሚሳካ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የግድቡ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ በዞኑ ከባለሀብቶች፣ ከመንግስት ሰራተኞች፣ ከአርሶ አደሮችና ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በቦንድ ሽያጭና በስጦታ መልክ ከ208 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ኃላፊው ጠቁመዋል።
እየተካሄደ ባለው ንቅናቄ በመሳተፍ ለግድቡ ግንባታ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ የሁለት ሺህ ብር ቦንድ የገዙት የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ሳሙኤል አባይነህ፤ የግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የአንድነታችን መገለጫ ለሆነው የህዳሴ ግድብ ትብብራችንን በማጠናከር ከድህነት ለመውጣት ልንተጋ ይገባል በማለት ገልጸዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ መሠለ ግርማ የራሳችንን ሀብት ተጠቅመን በቁጭት የጀመርነውን የግድቡን ግንባታ የታለመለትን ግብ እስኪመታ ድረስ ሁሉም በየአቅሙ አሻራውን ሊያስቀምጥ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ለፍፃሜ እስኪበቃ ድረስ በቦንድ ግዢ እንዲሁም ስጦታ መልክ በሌሎች መንገዶች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በዞኑ የአረካ ከተማ ነዋሪ የሆቴል ሥራ ባለሙያዋ ወይዘሮ እመቤት ደረሰ ለግድቡ ግንባታ የ500 ብር የቦንድ ግዢ መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
"ለኔም ሆነ የልጆቼን እጣ ፈንታ የሚወስን ታላቅ ፕሮጀክት በመሆኑ ተሳትፎዬን አላቋርጥም" ብለዋል።
ሌላኛው የቦዲቲ ከተማ ነዋሪ ወጣት አንዱዓለም ጌቱ ታሪካዊ በሆነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ እኔም የድርሻዬን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ ብሏል።
በመሆኑም በተጀመረው የአንድ ወር ንቅናቄ በመሳተፍ የ1 ሺህ 500 ብር ቦንድ መግዛቱን ተናግሯል።