የሃይማኖት ተቋማት ፍቅርንና አብሮነትን በመስበክ ለኢትዮጵያ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና ማጠናከር ይገባቸዋል-ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት ተቋማት ፍቅርንና አብሮነትን በመስበክ ለኢትዮጵያ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና ማጠናከር ይገባቸዋል-ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 28/2015 (ኢዜአ)፡- የሃይማኖት ተቋማት ፍቅርንና አብሮነትን በመስበክ ለኢትዮጵያ ሰላም መረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና ማጠናከር እንደሚገባቸው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ አስታወቁ፡፡
በኢትዮጵያ በየዘመናቱ የሃሳብ ልዩነቶች በውይይት ከመፈታት ይልቅ የግጭት መነሻ እየሆኑ ሰላምን ሲያደፈርሱና በዚህም ለሰላማዊ ዜጎች ሞት፣ መፈናቀል እንዲሁም ለንብረት ውድመት ምክንያት ሲሆኑ ተስተውሏል።
መንግሥት እነዚህ ስር የሰደዱ እና የግጭት መነሻ የሚሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ በሀገሪቱ የትኛውም አካባቢ የሀሳብ ልዩነት አለን የሚሉ አካላት አጀንዳዎቻቸውን ለውይይት አቅርበው በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ በማቅረብ ላይ ነው።
ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ሂደትም ማህበረሰቡ፣ የሃይማኖት ተቋማት እና የፖለቲካ ልሂቃን የየራሳቸው ድርሻ እንዳላቸው ይታመናል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ዘላቂ ሰላምን የማረጋገጥ ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም ብለዋል።
በተለይም የሃይማኖት ተቋማት ስለፍቅርና እርስ በርስ መዋደድ በማስተማር ለሀገር ሰላም መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
"የሰላም አስፈላጊነት ልክ እንደምንተነፍሰው አየር ነው፣ ያለ አየር በህይወት መቆየት እንደማይቻል ሁሉ ሰላም ከሌለ ወጥቶ መግባትም ሆነ ሀገርን ማልማት አይቻልም" ብለዋል፡፡
ስለሆነም ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ለምዕመኖቻቸው ከሚሰጡት ሃይማኖታዊ ትምህርት በተጨማሪ ስለፍቅርና ሰላም በመስበክ የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
በስነ-ምግባርና ሞራል የታነፀ ዜጋ ማፍራትና ግብረ-ገብነት የተላበሰ ትውልድ መፍጠር ለመንግሥት ብቻ የተተወ ባለመሆኑ የሃይማኖት ተቋማትም የድርሻቸውን መውሰድ እንደሚገባቸው በመጠቆም፡፡
የሃሳብ ልዩነቶች ተፈጥሯዊ ናቸው ያሉት ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ፤ ነገር ግን ዜጎች ይህንን የሃሳብ ልዩነት የግጭት መነሻ ማድረግ እንደሌለባቸው አመላክተዋል፡፡
የትኛውንም አይነት ልዩነት የጸብ ምንጭ ከማድረግ ይልቅ ቁጭ ብሎ በመወያየት መፍታት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ማህበረሰቡም ሰላምን የማረጋገጥ ጉልህ ሚናውን እንዲወጣ ጠቁመዋል፡፡
የፖለቲካ ልሂቃንም የሃሳብ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እና ምክክር የመፍታት ባህልን ማዳበር ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።