"እንሰትና ሁለገብ ጠቀሜታው"

1083

በፍሬዘር ጌታቸው

እንሰት በኢትዮጵያ ከ10 ሺህ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ፤ በተለይ በደቡቡ የሀገሪቱ ክፍሎች በስፋት የሚመረት ተክል እንደሆነ የታሪክ ድርሳናትና በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ያስረዳሉ። እንሰት በደቡብ የሀገራችን ክፍል በሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝብች ዘንድ በስፋት የሚታወቅ ነውና የምግብ ዋስትና አለኝታ ተደርጎ የሚወሰድ ተክል ነው። ተፍቆ ለምግብነት ወሳኝ የጤንነት መጠበቂያና የጥንካሬ መሰረት ተደርጎ ይወሰዳል። የእንሰት ተክል የሚጣል ነገር የለውም። ተረፈ ምርቱ ለእንሰሳት መኖ ጭምር ያለው ፋይዳ የላቀ ነው። እያንዳንዱ የእንሰት ተክል ክፍል ከምግብነት ባሻገር ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውላል።

የእንሰት ተክል ለም አፈር በንፋስና በጎርፍ ታጥቦ እንዳይወሰድ የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ ነው። ከዚህም ባሻገር  የአፈር ለምነትን እና እርጥበት ጠብቆ በማቆየት ለምርታማነት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ከደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች ሕዝቦች ጋር ያለውን ቁርኝት ዘመን ተሻጋሪ ያደርገዋል። 

ለአብነትም እንሰት በወላይታ ብሄር ከሰውና ከእንስሳት ምግብነት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን በአካባቢው "ኡታ" ተብሎ ይጠራል። እንሰት ወይም "ኡታ" የባለፀጋነት መገለጫም ነው። የመኖሪያ ቤቱን ዙሪያ፣ ቀዬውን በእንሰት የከለለና ያስዋበ፣ ማሳውን በእንሰት ያለማ አባወራ ባለጠጋ እንደሆነ ይታመናል። አባወራውም "አላ ኡታ ጎዳው" በማለት ይሞካሻል። እንሰት   ለምግብነት፣ ለመደኃኒትነት፣ ለአካባቢ ውበት፣ ለአፈር እርጥበትና ለምነት ለመጠበቅ፣ ለእንሰሳት መኖነት፣ ለባህላዊ ቤት ስራ ጣራና ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ያገለግላል። 

እንዲሁም ኮባው (ቅጠሉ) እንደ ዳቦ ለመሳሰሉት ምግብ ማብሰያና ለተለያዩ የግብርና ዉጤቶች መጠቅለያነት ግልጋሎት ይውላል። ከእንሰት ተረፈ ምርቶች የመቀመጫና የወለል ምንጣፎችን ጨምሮ በርካታ መገልገያዎች ይሰራሉ። የእንሰት ተክል በተለያዩ አካባቢያዊ ሁኔታ መብቀል ከመቻሉ ባሻገር ድርቅን የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ ነው። በዚህም አካባቢው ላይ ድርቅ በተከሰትበት ወቅት "ነፍስ አድን" የሚል ስያሜም ተሰጥቶት እንደነበር በታሪክ ይናገራል። 

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለሰ መኮንን እንሰት ምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና የልማት ችግሮችን ከማቃለል  አንጻር ከፍተኛ ሚና ያለው ነው ይላሉ። ተክሉ በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብና በሲዳማ ክልሎች በስፋት እንደሚለማና በሀገሪቱ ከ3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በተለያየ የእንሰት ዝርያ መሸፈኑን ያስረዳሉ። 

ከሀገሪቱ ህዝቦች ከ25 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የእንሰት ተዋፅኦን የሚመገቡና የሚገለገሉ ናቸው። የእንሰት ተክል በባህሪው የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም የከፍተኛ አቅም ያለው በመሆኑ፤ ለዝናብ እጥረትና ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ተክሉን በስፋት በማልማት የምግብና ዋስትናን በዘላቂነት ማረጋገጥ ይቻላል ይላሉ። እንሰትን ለምግብነት ከመጠቀም ባሻገር ለገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ትልቅ ሀብት በመሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀም የተሻለ አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል ሲሉ ያስረዳሉ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር መለሰ። 

እንሰት በአካባቢው ማስገኘት ከሚገባው ጠቀሜታ አንፃር ሲታይ እየሰጠ ያለው ጥቅም ከአቅም በታች ነው የሚሉት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የእንሰት ሰብል ተመራማሪ ዶክተር አብርሃም ቦሻ ናቸው። በመሆኑም የእንሰትን ምርታማነት ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲው የምርምር፤ የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን በትኩረት እየሰራ ነው ይላሉ። በኢትዮጵያ ከባህር ጠለል በላይ ከ1 ሺህ 500 እስከ 3 ሺህ 100 ሜትር ከፍታና አማካይ የዓመት ዝናብ መጠን ያለው አካባቢ ለእንሰት ተክል ምቹ ሲሆን፤ እንሰት ዝናብን የሚተካ አማራጭ የውሃ ምንጮች ባሉበት አካባቢ ከ1 ሺህ 500 ሜትር በታች በሆኑ ቆላማ አካባቢዎችም ምርት ሊያስገኝ ይችላል ይላሉ። 

እንደ ተመራማሪው ገለጻ እንሰት በሀገሪቱ ከሚገኙና ዋና ዋና ሰብሎች ከሚባሉት መካከል አንዱና ከ10 ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ ያለው ነው። ተክሉ ተራራማ ቦታዎች ላይ ጭምር በምቾት የሚያድግ ሲሆን እንደ ዝርያው ዓይነት ከሶስት እስከ አምስት ዓመት ውስጥ ምርቱ ውጤታማ መሆን ይችላል። ዝርያው "ወንዴ" እና "ሴቴ" ተብሎ የሚከፈል ሲሆን፤ 60 ያህል የእንሰት ዝርያዎች አሉ። ከምርት አያያዝና ብቃት አንጻር ሲታይ ከእያንዳንዱ የእንሰት ተክል ከ40 ኪሎ በላይ ዱቄት ይገኝበታል። 

እንሰት ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ጉልህ አስተዋፅኦ ያለው ሰብል ነው፤ ከዛም አልፎ ለሰውና ለእንስሳት ከተለያየ በሽታ የመከላከልና ከጉዳት ለማገገም የሚያስችል መድኃኒት ነው። ተክሉን የማባዛት ስራ በባህላዊ መንገድ የሚከወን ሲሆን፤ የእንስሳትና ሌሎች የሚወገዱ ተረፈ ምርቶችን በመጨመር እድገቱን ውጤታማ ማድረግ ይቻላል። ከእንሰት ምርት የሚገኘው ዱቄት ቡላ ወይም በአካባቢው አጠራር "ኢቲማ" ለልጆችና ለአዋቂዎች ጤና ተስማሚ ሲሆን፣ ገንፎ፤ የክትፎ የአይብና ጎመን ማባያ ቆጮ "ኡንጫ" እንዲሁም ሙቾና ባጭራ ለምግብነት ከሚውሉት ተጠቃሽ ናቸው።  የእንሰት ተክል በተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ላይ የሚለማ፣ የአየር ንብረት ለውጡን የመቋቋም አቅም ያለው  ተክል ነው። 

የወላይታ ዞን እንሰት አብቃይ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ ሲሆን በተለይም በባይራ ኮይሻ፣ በቦሎሶ ሶሬና በአንዳንድ የሶዶ ዙሪያ ወረዳዎች በተደረገ የዳሰሳ ጥናት የእንሰት ተክል የመመናመንና የበሽታ አደጋ እንደተጋረጠበት ዶክተር አብርሃም አብራርተዋል። ለዚህም ምርቱን መልሶ ለማስፋፋትና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ከዞኑ ግብርና መምሪያ ጋር በመሆን በትብብር እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ። 

የወላይታ ዞን የግብርና መምሪያ እርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አሸናፊ ዓለሙ እንዳሉት በወላይታ ዞን ከ28 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በእንሰት ተክል የተሸፈነ ነው። የእንሰት ተክል የሚፈለገውን ምርትና ውጤት እንዳይሰጥ ከሚያደርጉ ተግዳሮቶች መካከል ዋነኞቹ የአጠውልግና የአምቾ አበስብስ በሽታ፣ የተለያዩ ተባዮች፣ ፍልፈልና ጃርት ይጠቀሳሉ። 

የእንሰት አጠውልግና የአምቾ አበስብስ በሽታ በሁሉም የእንሰት አብቃይ ስነ-ምህዳር የሚገኝ፣ በሁሉም የእድገት ደረጃ ላይ ያለን የእንሰት የሚያጠቃና ከአንዱ ወደ ሌላው ተክል የሚተላለፍ መሆኑ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል። በመሆኑም ችግሩን ለማስወገድ ጤነኛ የእንሰት ተክሎችን በላቦራቶሪ የማባዛት፣ የበሽታ አምጪ ተህዋሲያን የማጥናትና በጄኔትክ ምህንድስና በሽታን የሚቋቋም ቅንጣት ወደ እንሰት የማስገባት ሥራ እየተሰራ ነው። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፣ ከሶዶ ግብርና ኮሌጅ እንዲሁም ከአረካ የምርምር ማዕከል ጋር በመሆን በጋራ  እየተሰራ ነው። 

ኃላፊው እንዳስረዱት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በሽታን የሚቋቋሙ ከ20 ሚሊዮን በላይ የእንሰት ችግኞችን አባዝቶ በመትከል የተሻለ ውጤት እየታየ ነው። ይህን ሥራ በማጠናከር ከእንሰት ዘርፍ ሊገኝ የሚገባውን ጥቅም ለማግኘት አርሶ አደሩ ያለውን አገር በቀል ዕውቀቱን በአግባቡ እንዲጠቀም በከፍተኛ ንቅናቄ እየተሰራ ይገኛል። በዚህም የአካባቢውን የእንሰት ሽፋን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን የአርሶ አደሩን ጥያቄ መመለስና ጥቅሙን ለማላቅ የተጀመረው የንቅናቄ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ወሳኙ ስራ ተደርጎ እየተከናወነ ነው። ማህበረሰቡ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም